ደባርቅ ከተማን በማልማት የቱሪዝም ሀብቷን ለዓለም መግለጥ ይገባል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ደባርቅ ከተማን በማልማት የቱሪዝም ሀብቷን ለዓለም መግለጥ ይገባል - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦ የመቻቻልና የመረዳዳት ማዕከሏን ደባርቅ ከተማን በማልማት የቱሪዝም ሀብቷን ለዓለም መግለጥ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የደባርቅ ከተማን ለማልማት የተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር "ደባርቅን እናሳምር ከተማችንን እናድምቅ" በሚል መሪ ሀሳብ በሂልተን ሆቴል እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሀብቶች ተገኝተዋል።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ "ኑ ተፈጥሮ የገለጠችውን ድንቅ የቱሪስት መስህብ ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መግቢያ በር የሆነችውን ደባርቅ ከተማ በጋራ እናልማ" የሚል ጥሪ ቀርቧል።
ደባርቅ ከከተማም ባሻገር የኢትዮጵያን ፀጋ እያፈካ ያለው የቱሪዝም፣ የጥበብና የዳጎሰ ታሪክ መገኛ ምድር ናት።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘውን ብርቅየውን ዋሊያ አይቤክስ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቀይ ቀበሮ ለማየት መሸጋገሪያ ድልድይ ሆና ታገለግላለች።
ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በስሩ ካሉት 530 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች 75ቱ፤ በፓርኩ ከሚገኙ 217 የዓዕዋፍ ዝርያ ውስጥ 10 በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ከተሜነት ዘመናዊ ዕሳቤን ያሳድጋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች ከዚህም በላይ በቴክኖሎጂ ዳብረው መዘመን እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ቢሆንም በመሰረተ ልማትና መሰል ችግሮች የሚገባውን ያህል ጎብኚ እያስተናገደ አይደለም ብለዋል።
በመሆኑም የመቻቻልና የመረዳዳት ማዕከሏን ደባርቅ ከተማን በማልማት የቱሪዝም ሀብቷን ለዓለም መግለጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ደባርቅ ጥሪቶች ያሉባት መሆኑን ገልጸው፤ ዓለም ዓይኑን እንዲገልጥ ከተማዋን ማዘመን ይገባል ነው ያሉት።
በዚህም ይሄንን ድንቅ አካባቢ ለማልማት ማገዝና መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።