ቀጥታ፡

በአስተዳደሩ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን በትምህርት ገበታ ለማሳተፍ ምዝገባ ተጀምሯል-መምሪያው

ሰቆጣ ፤ነሐሴ 18/ 2018 (ኢዜአ )፡-በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ20 ሺህ በላይ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናትን በትምህርት ገበታ ለማሳተፍ ምዝገባ መጀመሩን የብሄረሰቡ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2019 ትምህርት ዘመን ውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራ ለማከናወን ያለመ የንቅናቄ መድረክ በሰቆጣ ከተማ አካሂዷል።

የንቅናቄ መድረኩን የከፈቱት የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሹመት ጥላሁን እንደገለጹት፤ ውጤታማና የተማረ ዜጋን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የሁሉም ርብርብ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።


 

በብሔረሰብ አስተዳደሩ ባለፈው ትምህርት ዘመን የጸጥታ ችግሮችን በመቋቋም በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡ መሆኑን አመልክተዋል።

በአዲሱ ትምህርት ዘመንም የሕፃናትን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በርብርብ ሊሠሩ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የብሔረሰብ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፍትሐለሽ ምረቴ እንዳሉት፤ 280 ሺህ 293 ተማሪዎችን ለማስተማር ምዝገባ መጀመሩን ተናግረዋል።

ወደ ትምህርት ገበታ ለመምጣት ከሚመዘገቡት ውስጥ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑት እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕፃናትን በትምህርት ገበታ ለማሳተፍ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲሱ ትምህርት ዘመን ውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራ ለማከናወን የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተከናውነዋል  ነው ያሉት።

የትምህርት ባለድርሻ አካላትና ወላጆች በወቅቱ ልጆቻቸውን እንዲያስመዘግቡም ጥሪ አቅርበዋል።

የጋዝጊብላ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳነ ሙሉ በበኩላቸው፤ የጸጥታ ችግርን በመቋቋም በ40 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራ እየተከናወነ እንደነበር አውስተዋል።

በ2019 ትምህርት ዘመን የተሳካ የመማር ማስተማር ሥራ ለማከናወን ማህበረሰቡን ያሳተፉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

በወረዳው የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን በግብዓትና ምቹ ከባቢ የሚፈጥሩ ተግባራት በክረምት ወራት ተሠርቷል ያሉት ደግሞ የዝቋላ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ የፀዳው ገዳሙ ናቸው።

በአዲሱ ትምህርት ዘመን ተማሪዎችን በአጭር ጊዜ መዝግቦ ለማጠናቀቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በርብርብ እየተሠራ ነው ብለዋል።

የአምደ ወርቅ አንደኛ ትምህርት ቤት የተማሪ ወላጆች ተጠሪ አቶ ሙሉ ዘነበ፤ ተማሪዎች በወቅቱ እንዲመዘገቡ ከማድረግ አንፃር የወላጆች ድርሻ የጎላ ነው።

ይህም ተማሪዎች በወቅቱ ተመዝግበው በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም