ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ሽንፈትን አስተናገደ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የምድብ ሁለት መርሐ ግብር የዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 1 ለ 0 አሸንፏል።

ማምሻውን በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አግነስ ናቡኬንያ በ11ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ግቧን አስቆጥራለች።

በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈቱን ተከትሎ ወደ ግማሽ ፍጻሜ የማለፍ እድሉ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።

ንግድ ባንክ በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታው የጅቡቲውን ኡጄኮን 11 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ቡድኑ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ በመጨረሻው የምድብ ጨዋታ ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስን በኡጄኮ መሸነፍ ይኖርበታል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ረቡዕ ነሐሴ 2018 ዓ.ም በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይካሄዳል።

ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ በጨዋታው ካሸነፈ ወይም አቻ ከወጣ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያልፋል።

የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሩዋንዳ ኪጋሊ እየካሄደ ይገኛል።

በውድድሩ ላይ 10 ክለቦች በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።

የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ውድድሩን ያሸነፈው ክለብ ዞኑን ወክሎ በሻምፒዮንስ ሊጉ መሳተፉን ያረጋግጣል።

የሴካፋ ማጣሪያ እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም