በክልሉ በፓርቲው መሪነት በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በፓርቲው መሪነት በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ውጤት ተመዝግቧል
ሳውላ፤ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በብልጽግና ፓርቲ መሪነት በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የ2018 በጀት አመት አጠቃላይ የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀምና የ2019 ዕቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በሳውላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በፓርቲው መሪነት የተከናወኑ የልማት ኢንሼቲቮችና የንቅናቄ አጀንዳዎች የተሳኩና ውጤት የተገኘባቸው ናቸው።
በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የታየውን ስኬት ለአብነት ጠቁመው በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብርም አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል ።
በተመሳሳይ በኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሀገር ውስጥ ምርትን በመተካት እንዲሁም ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ እመርታ መመዝገቡን አመልክተዋል ።
በክልሉ ከተሞች የኮሪደር ልማት በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በተመሳሳይ መልኩ የገጠሩን ሕብረተሰብ የኑሮ ዘይቤ በዘላቂነት ለመቀየር የተጀመረው ሞዴል የገጠር ኮሪደር ልማት ስራም ውጤታማ መሆኑን አንስተዋል ።
ባጠቃላይ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ባስገኛቸው ውጤቶች ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በማህበራዊ ልማት በኩል በትምህርትና በጤና ዘርፎች ጥራትን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውንም አንስተዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአረጋውያንና አቅም ለሌላቸው ወገኖች የተደረጉ የቤት አድሳትና የድጋፍ ስራዎች ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍ ባህልን ያጎሉ፣ የእርሰ በርስ መስተጋብርን ያጠናከሩ ናቸዉ ብለዋል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸዉ በፓርቲዉ መሪነት በበጀት ዓመቱ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ይህም በዞኑ ዜጎችን በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ ማድረጉን ጠቁመው በህዝብ ተሳትፎ ውጤቱን ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል ።
በመድረኩ በብልጽግና ፓርቲ የክልል፣ የዞኖችና የከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።