በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የሕዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው
ሳውላ፣ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመደመር መንግስት እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸውን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።
አቶ ገብረመስቀል ጫላን ጨምሮ ከክልሉና ከዞኖች የመጡ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በጎፋ ዞን እና በሳውላ ከተማ በመደመር መንግስት እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል።
አቶ ገብረመስቀል በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ በመደመር መንግስት እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ነው።
በክልሉ ጎፋ ዞንም በግብርናና በኮሪደር ልማት የተከናወኑ ተግባራት የዜጎችን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በእንስሳት እና በዶሮ እርባታ ዘርፍ እየተተገበሩ ያሉ ሥራዎች ውጤታማ ናቸው ያሉት አቶ ገብረመስቀል፣ በዘርፉ የተሰማሩ ዜጎችም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
በተለይ በሳውላ ከተማ በወተት እና በወተት ተዋጽኦ ምርት ላይ የተሰማሩ ወጣቶች ካፒታላቸውን ከ64 ሺህ ብር መነሻ ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ማሳደገቻው ለሌሎች ተሞክሮ ይሆናል ብለዋል።
በክልሉ ለሚያጋጥሙ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችም በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አቶ ገብረመስቀል አያይዘው ጠቅስዋል።
በተለይም ካለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ ሀብት የማሰባሰብና ሰብል የማምረት ሥራው ተጠናክሮ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት።
በጎፋ ዞን ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ደግሞ የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ናቸው።
ተደራጅተው በሌማት ትሩፋት መርሀግብር ወደሥራ የገቡ ወጣቶች ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር መቻላቸውን ገልጸዋል።
በዞኑ በተለይ በዶሮ እርባታ፣ በማር ምርት፣ በወተት ልማትና በሌሎችም ዘርፎች የመጣውን ውጤት ለማስቀጠል ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
ከሦስት ዓመት በፊት በ64 ሺህ ብር መነሻ ካፕታል የአንድ ቀን የዶሮ ጫጩቶችን እርባታ ሥራ እንደጀመሩ የተናገረው ደግሞ ወጣት ሰላሙ ዮናስ ነው።
በሂደት ሥራቸውን ወደ ወተት ላም እርባታ ሥራ እንደቀየሩ ገልጾ በአሁኑ ወቅትም ለሳውላ ከተማ ነዋሪዎች የወተት ምርታቸውን በስፋት እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግሯል።
የወተት ላሞቻቸው ቁጥር ከ8 በላይመድረሱን የገለጸው ወጣት ሰላሙ፣ ካፒታላቸውም ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱንና ለአምስት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም አስረድቷል።
ሥራቸውን በማስፋፋት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆንም የእንስሳት መኖ ልማት ሥራ እንደጀመሩ ጠቁሞ፣ በመንግስት እየተደረገላቸው ያለ ድጋፍ ለውጤታማነታቸው አጋዥ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቋል።