በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-አቶ ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦በሀረሪ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እየተሰሩ የሚገኙ ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ የሀረር ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታን ጨምሮ በክልሉ እየተገነቡ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በዚህ ወቅትም እንዳሉት፥በክልሉ በተለይም የትምህርት ጥራት ለማሳደግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እያገኙ ይገኛሉ።
ለዚህም ክልሉ በ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 22 ነጥብ 76 ተማሪዎችን በማሳለፍ ከአገር አቀፍ ደረጃ 2ኛ በመውጣቱ አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የተማሪዎች ውጤትን ለማሻሻል እየተከናወኑ ከሚገኙ ስራዎች ባሻገር የትምህርት መሰረተ ልማትን በማሳደግ ጥራት ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ፋይዳቸው ከፍ ያለ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ግንባታው እየተፋጠነ የሚገኘው የሀረር ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታም ለዘርፉ ውጤታማነት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅና በ2019 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ከግንባታ ጎን ለጎንም የሰው ሀይልና ግብዓት የማሟላት ስራ መጀመሩን ነው የገለፁት።