በሀገራዊ ምክክሩ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ በመመካከር ወደ መግባባት መሸጋገር የተቻለበት ነው – ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክሩ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ በመመካከር ወደ መግባባት መሸጋገር የተቻለበት ነው – ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የልዩነት ምንጭ በነበሩ አጀንዳዎች ላይ በግልጽነት በመመካከር የጋራ መፍትሔ ሀሳቦች የተቀመጡበትና ወደ የጋራ መግባባት መምጣት የተቻለበት ወሳኝ መድረክ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋና ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ባለፈው ቅዳሜ ተከናውኗል።
ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ማጠቃለያ በኋላ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመካካሪዎች እንዳሉት፤ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ በመመካከር ዘላቂ ልማትና ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ምክረ ሀሳቦችን በማፍለቅ ምክክራቸውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።
ከሶማሌ ክልል የተወከሉት ተመካካሪ አብዱልቃድር መሐመድ እንዳሉት፤ ምክክሩ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ተመካካሪዎች በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲያነሱና እንዲመካከሩ ዕድል ፈጥሯል።
መሰል የምክክር ሂደት በቀጣይም ሊገጥሙን ለሚችሉ ችግሮች መፍቻ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በምክክር ሂደቱ የተለያዩ ሀሳቦች ቀርበው ልዩነቶችን በምክክር በማቀራረብ ወደ የጋራ መግባባት መምጣት ተችሏል ብለዋል።
ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብን በመወከል የተመካከሩት መቶ አለቃ ዘለቀ ጮቅሬ፤ ምክክሩ የሀገሪቱን ሰላምና አንድነት ዘላቂ በማድረግ ለሁለንተናዊ ዕድገት የሚያግዝ ሂደት እንደነበር ገልጸዋል።
በምክክር ጉባኤው የልዩነት ምንጭ በነበሩ አጀንዳዎችና ኢትዮጵያ ወደፊት በሰላም እንዴት መቀጠል እንዳለባት በሰፊው መመካከራቸውንም አክለዋል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን አሸናፊ ለማድረግና ሰላሟንና ልማቷን በዘላቂነት ማስቀጠል የሚያስችል ግልጽና አሳታፊ ምክክር አድርገናል ብለዋል።
ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕናን የወከሉት ተመካካሪ ጌታቸው ዮሐንስ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የተስፋ ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ ገልጸዋል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሂደት ኢትዮጵያውያን ስለሀገራቸው የወደፊት አቅጣጫ በመመካከር፣ ችግሮቻቸውን ግልጽና አሳታፊ በሆነ መልኩ በማንሳት መፍትሔ የሚሆኑ ምክረ ሀሳቦችን ያቀረቡበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በምክክሩ የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ለቀጣይ ሀገራዊ ሥራዎች ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
መንግሥትም ምክረ ሀሳቦቹን እንደግብዓት በመጠቀም የሕዝቦችን አንድነት የሚያጎለብቱና ለጋራ ራዕይ የሚያነሳሱ እርምጃዎችን እንዲወስድ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተመካካሪው ገልጸዋል።