ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሆርቲካልቸር ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብት ምቹ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አቅም አላት - የሕንድ ባለሀብት ጋጄንድራ ሲንግ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአትክልትና ፍራፍሬ የግብርና ልማት ዘርፍ ዓለም አቀፍ የገበያ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብት ምቹ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩት የሕንድ ባለሀብት ጋጄንድራ ሲንግ ገለጹ።  

ጋጄንድራ ሲንግ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ቦዲቲ አካባቢ በአቮካዶ ልማት ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ።

በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍም በበርካታ ሀገራት የገበያ ጥናት በማካሄድ ለሆርቲካልቸር ዘርፍ ባላት ምቹ የተፈጥሮ ሁኔታና ጠንካራ የመንግሥት ድጋፍ ምክንያት ኢትዮጵያን መምረጣቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ምቹ የግብርና ኢንቨስትመንት ምኅዳር መሰረት ያደረገ የአዋጭነት ጥናት በማካሄድ በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ በተለይም በሆርቲካልቸር ዘርፍ ያላት ከፍተኛ የመልማት አቅም በመጠቀም ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ በማድረግ የሚጠቀሙበት ዕድል የተፈጠረባት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ካለው የሀገር ውስጥ ገበያ ባለፈ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ገበያ ምርቶችን ማቅረብ የሚያስችል የልማት ከባቢ መፈጠሩንም አስገንዝበዋል።

መንግሥት በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረገ ነው ያሉት ጋጄንድራ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢንቨስትመንት የሰጠው ቁርጠኝነትም ምቹ የልማት ምኅዳር ፈጥሯል ብለዋል።

በአዲስ አበባ እየተሠራ ያለው ሥራ የከተማዋን ገጽታ ከማሻሻል ባሻገር፤ በቢሾፍቱ እየተገነባ ያለው ግዙፍ የአየር ማረፊያ የመንግሥት የልማት ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት በአቮካዶ ምርት ላይ አበረታች ተግባር እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በገበያ ተደራሽነት ላይም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በቡና ወጪ ንግድ ያላትን ልምድ በመጠቀም በሆርቲካልቸር ዘርፍ ግንባር ቀደም ላኪ የመሆን ዕድል እንዳላት አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም