ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው የጋራ መግባባትን የሚያጎለብት ተስፋን የፈነጠቀ የወል ትርክት መገንቢያ ድልድይ ነው - የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፣ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የጋራ መግባባትን የሚያጎለብት ተስፋን የፈነጠቀ የወል ትርክት መገንቢያ ድልድይ መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአርባ ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

በነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም የማጠቃለያ መርሐ ግብር በተካሄደለት የምክክር ጉባኤም በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ጉዳይ መክረዋል፤ ኢትዮጵያም አሸንፋለች።

ይህም ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቁ የአለመግባባት ስብራቶችን በሐሳብ የበላይነት ላይ በተመሠረተ ጥበብ መፍትሔ መስጠት እንደሚችሉ ተስፋ የተጣለበት ውጤት አምጥተዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንዳሉት፤ የምክክር ጉባኤው ሰላምና ልማትን የሚያሳልጥ የሐሳብ ድልድይ የተገነባበትና የጋራ መግባባት መንገድን፣ የመደማመጥና የጋራ ራዕይ መድረክ ነው።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወጣት ናታን ከፋለው፣ የምክክር ጉባኤው እኛ ኢትዮጵያውያን በራሳችን ጉዳዮች ላይ በመምከር የጋራ መፍትሔ መስጠት እንደምንችል በተግባር ያስመሰከረ ነው ብሏል።

የጉባኤው ምክረ ሐሳቦችም በሐሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የጸናች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችሉ የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ መሆናቸውን ገልጿል።

በተለይም አሰባሳቢና የወል ትርክት ግንባታን በመገንባት በሕዝብና በመንግሥት መካከል ጠንካራ የመተማመን ድልድይ ለመገንባት ዕድል የሚሰጥ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ተናግሯል።


 

የልፍዋጋሽ ጫኔ በበኩላቸው፣ የምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚያንጽ የወል ትርክትን መገንባት የሚያስችል የምክክር ባህል መሠረት የተጣለበት መሆኑን ገልጸዋል።

በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ የወል ትርክት ግንባታም እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የፈለቁ ምክረ ሐሳቦችም በጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ የተመሠረተ ልማትና ዕድገትን ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።


 

ሌላኛው የመዲናዋ ነዋሪ ፓስተር መርዕድ ኃይሌ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የምክክር ምኅዳር ባለመፈጠሩ በዜጎች መካከል የጋራ መግባባትን መገንባት ሳይቻል ቆይቷል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤም የዜጎችን ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያስቀጥሉ ወሳኝ ምክረ ሐሳቦች የተንሸራሸሩበት መሆኑን ገልጸዋል።

የምክክር ጉባኤውም ዘላቂ ሰላምና ዕድገትን በማስፈን የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማሸጋገር የሚያስችል ዕድል ፈጥሮ ያለፈ የጋራ መግባቢያ ድልድይ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ጉባኤው በዜጎች መካከል የቆዩ የአለመግባባት ችግሮችን የጋራ መፍትሔ ማበጀት የሚያስችሉ ምክረ ሐሳቦች የፈለቁበት ነው ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ ወጣት ቃልኪዳን አድማሱ ናት።

የምክክር ጉባኤውም ለተሻለች ኢትዮጵያ ግንባታ ጠንካራ መሠረት ከመጣሉ ባሻገር ለወጣቶችና ለሁሉም ዜጎች የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመልክታለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም