የጋራ ሀገራዊ ራዕይ ለመቅረፅ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተው -የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
የጋራ ሀገራዊ ራዕይ ለመቅረፅ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተው -የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የልዩነት ምንጭ በነበሩ መሰረታዊ አጀንዳዎች ላይ በመመካከር የወደፊት የጋራ ሀገራዊ ራዕይ ለመቅረጽ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለአርባ ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም. የማጠቃለያ መርሐ ግብር በተካሄደለት የምክክር ጉባኤም፣ በስምንት ዐበይት አጀንዳዎች ላይ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ጉዳይ መክረዋል፤ ኢትዮጵያም አሸንፋለች።
ይህም ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የዘለቁ የአለመግባባት ስብራቶችን በሐሳብ የበላይነት ላይ በተመሠረተ ጥበብ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ውጤት አምጥተዋል።
በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ የምክክር ጉባኤው በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ መሠረታዊ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የተመከረበት ነበር።
በዚህም በሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ የልዩነት ምንጭ ሆነው ለቆዩ አጀንዳዎች ላይ በመመካከር፣ የጋራ የወደፊት ራዕይ ለመቅረጽ ትልቅ ምዕራፍ የከፈተና ለመጪው ትውልድ ጠንካራ መሠረት የተጣለበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነበር ብለዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ታረቀኝ አብዱጀባር እንዳሉት፣ በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሁሉም ሰው የራሱን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ጥያቄዎች ያዳመጠበትና የጋራ ምክረ ሐሳብ ያቀረበበት ጉባኤ እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህም ተመካካሪዎች በስምንቱም አጀንዳዎች ላይ በመመካከር፣ የጋራ ስምምነት ላይ በመድረስ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተርፍ አዲስ ተስፋና መሠረት መጣሉን ጠቁመዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ኤሊያስ ደባሱ በበኩላቸው፣ የምክክር ሂደቱ ከወረዳ ጀምሮ ሁሉንም አካላት ባካተተ መልኩ መካሄዱን ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያ ማሸነፏ በተግባር የታየበትና ለአፍሪካ ተምሳሌት የሚሆን ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊ መልክ ያለው ሐሳብ የተንጸባረቀበት ጉባኤ እንደነበር በመግለጽ፣ ይህ ምክክር ሀገራችንን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ትልቅ አርአያ የሚሆን ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ተመካካሪው አቶ ስዩም ዮሐንስ እንደገለጹት፣ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ በመመካከር ሀገርን የሚያሻግሩ ምክረ ሐሳቦች መቅረባቸውን አብራርተዋል።
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ላለፉት ዘመናት የልዩነት ምንጭ ለነበሩ ጉዳዮች የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦችን ከማስቀመጥ ባለፈ፣ በቀጣይ ሊገጥሙ ለሚችሉ መሰል ጉዳዮች የመፍቻ ስልት የተቀየሰበት እንደነበርም ጠቅሰዋል።
በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የጸደቁ ምክረ ሐሳቦች ወደ ተግባር ሲተረጎሙ፣ የምክክር ሂደቱ ውጤት ይበልጥ ተጨባጭ እንደሚሆን ገልጸዋል።
እነዚህ የቀረቡ ምክረ ሐሳቦች ወደ ተግባር እንዲገቡ ማድረግም የሚቀጥለው ቁልፍ ሥራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።