በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገር የማጽናት ትዕምርት - ኢዜአ አማርኛ
በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገር የማጽናት ትዕምርት
በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገር የማጽናት ትዕምርት - የሌተናል ኮሎኔል ምትኩ ገብሩ እና የኮማንዶ በረከት ምትኩ ታሪክ
ሀገርን በማገልገል የማጽናት ጉዳይ በአንድ ትውልድ ተጀምሮ የሚጠናቀቅ አይደለም፤ በትውልድ ቅብብሎሽ ሂደት እየደረጀ የሚዘልቅ እንጂ።
እሴት፣ አርበኝነት፣ ተግባራዊ ቁርጠኝነትና ስለሀገር የሚኖር የኃላፊነት ስሜት በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገርን በፍጹም ቁርጠኝነት ለማገልገል መነሳት፣ ሀገርን ለማጽናት ያለው ትርጉም የጎላ ነው።
በዚህ ጽሑፍ ሀገርን በትውልድ ቅብብሎሽ የማጽናት ትክክለኛ ትዕምርት የሆነውን የአባትና ልጅ እውነተኛ ታሪክ እናካፍላችኋለን። አባት ሌተናል ኮሎኔል ምትኩ ገብሩ፤ ልጅ ደግሞ ምክትል አሥር አለቃ በረከት ምትኩ ይባላሉ።
ሁለቱም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ሀገርን ለማጽናት በፍጹም ቁርጠኝነት በተመሳሳይ ሙያ ላይ ተሰማርተዋል።
አባት የወታደርነት ሙያን በመቀላቀል የሌተናል ኮሎኔልነት ደረጃ ደርሰው ሀገራቸውን እያገለገሉበት ያለውን ዳና ልጃቸውም እንዲጋራው በማድረግ፣ አሁን ላይ በመከላከያ ሠራዊት የኮማንዶ ክፍልን መርጦ በመቀላቀል ሀገሩን እያገለገለ ይገኛል።
አባት ሌተናል ኮሎኔል ምትኩ ገብሩ በረዥም የአገልግሎት ዘመናቸው የተማሩትን የሀገር ፍቅር፣ ጽናትና ሀገራዊ ኃላፊነት ልጃቸውም በራሱ መንገድ በመቀበል ከቤተሰብ ታሪክ በላይ ሀገርን ለማጽናት የትውልድ ቅብብሎሽን ትርጉም በተግባር አሳይተዋል።
በተለይም ልጃቸው ምክትል አሥር አለቃ በረከት ምትኩ የኮማንዶ ሥልጠና የሚጠይቀውን አካላዊ ዝግጁነት ሀገርን በቁርጠኝነት የማገልገል ተነሳሽነትና ጽናት፣ ትዕግሥትና ተልዕኮን በብቃትና በኃላፊነት የመወጣት መሻት የአባትና ልጅ ታሪክን ልዩ ያደርገዋል።
ይህ የአባትና ልጅ ታሪክ ወታደርነት አንድ ሙያ ወይም የሥራ መደብ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገርን በቁርጠኝነት፣ በጽናትና በታማኝነት ለማገልገል እንዲሁም የሀገርና የሕዝብን ደኅንነት በታማኝነት ለመጠበቅ የተገባ የባንዲራ ቃል ኪዳን ጥግ መሆኑን ያመላክታል።
አባት የጀመረውን ሀገርን በቁርጠኝነት የማገልገል እውነተኛ መንገድ ልጅ መቀጠሉ፣ ሀገር ጸንታ የምትኖረው በትውልድ ቅብብሎሽ መሆኑን በተጨባጭ ያሳያል።
አባት ሌተናል ኮሎኔል ምትኩ ገብሩ፣ ልጃቸው ሙሉ ስብዕናን ተላብሶ እንዲያድግና ሀገሩን በፍጹም ታማኝነትና ቁርጠኝነት እንዲያገለግል የውትድርና ሙያን እንዲቀላቀል ፍላጎት እንደነበራቸው ገልጸዋል።
በዚህም ልጃቸው ከነበረበት የደቡብ ዕዝ ወደ ልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሠልጠኛ ማዕከል እንዲቀላቀል በማድረግ የኮማንዶ ሥልጠናን ተከታትሎ እንዲመረቅ በማድረጋቸው ልዩ ደስታ እንደፈጠረላቸውና ፍላጎታቸው መሳካቱን ጠቁመዋል።
ልጃቸው ምክትል አሥር አለቃ በረከት ምትኩ፣ እንደ አባታቸው ወታደር በመሆን ሀገርን በታማኝነት ለማገልገል ትልቅ ሕልም እንደነበራቸውም ተናግረዋል።
ፈታኝ ውስብስብና ሁለንተናዊ ዝግጁነትን የሚጠይቀውን የኮማንዶ ሥልጠና አጠናቀው ለስኬት እንዲበቁ፣ አባታቸው ሌተናል ኮሎኔል ምትኩ ምክርና ጠንካራ ድጋፍ በመስጠት እንዳበረታቷቸው ገልጸዋል።
የእኔ ሀገርን የማገልገል ዘመን እንዳያቆም፣ የአብራኬን ክፋይ ተክቼ ሀገር እንዲጠብቅ በመተካቴ ታላቅ ኩራት ይሰማኛል ነው ያሉት።
ምክትል አሥር አለቃ በረከት ምትኩ በበኩሉ፤ የአባቱን የጀግንነት ገድልና ለሀገር ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር በተግባር እያየ ማደጉን ተናግሯል።
ከአባቱ የቀሰመውን ይህን ታላቅ ሀገርን በታማኝነት የማገልገል እሴት በመውረስ፣ በ2014 ዓ.ም የአባቱን ፈለግ በመከተል የመከላከያ ሠራዊቱን መቀላቀሉን ጠቁሟል።
የውትድርና ሕይወት ከፍተኛ ጽናትና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን ምክትል አሥር አለቃ በረከት ፈታኝ የሆነውን የኮማንዶ ሥልጠና በስኬት አጠናቆ ለምረቃና ሀገርን በቁርጠኝነት ለማገልገል መብቃቱን ገልጿል።
በቀጣይም ከአባቴ በቀሰምኩት ጽናትና ወታደራዊ ሥነ-ምግባር፣ ሀገሬን በታማኝነትና በቁርጠኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ብሏል።
የምክትል አሥር አለቃ በረከት ምትኩ የአባቱን ፈለግ መከተል፣ ሀገርን በጀግኖች ትውልዶች ቅብብሎሽ በጽኑ መሠረት ላይ የማኖር ትልቅ ማሳያ ነው።