ቀጥታ፡

ሰብዓዊነትና የሕሊና እርካታ የሚያጎናጽፈው በጎ ፈቃድ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰብዓዊነት፣ የሕሊና እርካታ፣ ሕዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነት መሆኑን በመዲናዋ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩ  ገለጹ።

በጎ ፈቃደኝነት ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር፣ የሰብዓዊነት እሴቶችን ከፍ የሚያደርግ እና ከቁሳዊ ጥቅም ውጭ የሆነ ጥልቅ የአዕምሮና የመንፈስ እርካታን የሚያጎናጽፍ ታላቅ ተግባር ነው።

ይህ ተግባርም የተደራጀ፣ ዓለም አቀፍ እና ስልታዊ ገጽታን ይያዝ እንጂ፤ መነሻው ግን የሰው ልጅ ለወገኑ ካለው ፍቅር፣ ርህራሄ እና የኅብረተሰብ ስሜት የሚመነጭ የውስጥ ኃይል ነው።

በጎ ፈቃደኝነት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በመላው ኢትዮጵያ ክረምትና በጋ ቅን ልብ ባላቸው ሰዎች የሚሰጥ ሠናይ ተግባር ነው።

በኢትዮጵያ ካለፉት ዓመታት ወዲህ በበጎ ፈቃድ ስራለዎች በርካቶች ዘንድ በመድረስ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እፎይታን በማጎናጸፍ ላይ ይገኛል።


 

በመካኒሳ አካባቢ ቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ ደረጃ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ በማስዋብ ተሰማርተው ያገኘናቸው በጎ ፈቃደኛ በሀይሉ ድሪባ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጎነት ሰብዓዊነት ነው።

በአካባቢ ጽዳትና ልማት ስራዎች፣ በደም ልገሳ፣ ትምህርት ቤቶችን በማስዋብ፣ ሰብዓዊ እርዳታዎች በማሰባሰብ እና በሌሎች የበጎ ፈቃደኛ ስራዎች ላይ በንቃት እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።

በጎ ፈቃደኝነት ሥራዎች የሰዎችን ደስታ ማየቴ የበለጠ እንድተጋ አድርጎኛል ብለዋል።

የቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ ደረጃ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቤቶችን በማስዋብ ላይ ያገኘነው በጎ ፈቃደኛ ይድነቃቸው ሸዋለም በፈቃደኝነት ማገልገል የአዕምሮ እርካታ እንደሚፈጥር ተናግሯል።

ለ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት መፍጠር የሚያስችል መሆኑን በማንሳት፤ የኢትዮጵያ ባህል የሆነው በጎ ፈቃደኝነት ቀጣይኖት ሊኖረው እንደሚገባ ገልጿል።


 

በትራፊክ ማስተናበር እና በሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች የሚሳተፈው ሌላው በጎ ፈቃደኛ ሲሳይ ተስፋዬ ህብረተሰቡንና ሀገሩን በበጎ ፈቃደኝነት ማገለግል ከጀመረ 18 ዓመታት እንዳስቆጠረ ተናግሯል፡፡

ከመደበኛ ሥራው ጎል ለጎን በክረምት እና በበጋ በሚከናወኑ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ንቁ ተሳትፍ ማድረጉን ገልጿል፡፡


 

የትራፊክ ፍሰት በሚበዛበት እግረኞች ከትራፊክ አደጋ ለመጠበቅ ሜክሲኮ ላይ በትራፊክ አስተናባሪነት እያገለገለች ያገኘናት በጎ ፈቃደኛ መታሰቢያ ምናለ፤ በጎ ፈቃደኝነት የህሊና ነጻነት መሆኑን ገልፃለች።


 

በጎነት ሰውን መርዳትና ሰብዓዊነት መሆኑን በማንሳት፤ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርባለች።

አዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት በረከት ቢርቢርሳ ከሰኔ ወር ጀምሮ በአዲስ አበባ ከ515 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛ አባላትን በማሳተፍ ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በትራፊክ ማስተናበር፣ ክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ ደም ልገሳ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ የቤት እድሳት እና በሌሎችም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች የወጣቶች ሚና እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

የወጣቶች የበጎ ፈቃደኝነት ተሳትፎ እያደገ መምጣት የዜጎችን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና መወጣቱን ገልጸው፤ የወጣቶች ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም