ቀጥታ፡

በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው የደረቅ ወደብ ተርሚናል የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና አለው

ደብረ ብርሃን፤ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው የደረቅ ወደብ ተርሚናል በክልሉ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገለጸ። 

በጠቅላላው 275 ሚሊዮን ብር ወጪ በደብረ ብርሀን ከተማ ለሚገነባው የደረቅ ወደብ ተርሚናል ዛሬ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ የግንባታ ሥራው በይፋ ተጀምሯል።


 

በማስጀመሪያ መርሀግብሩ ላይ የአማራ ክልል መንገድ፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ቢሮ ሃላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የደረቅ ወደብ ግንባታው በክልሉ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ሥራዎች ለማሳለጥ ያግዛል።

በቢሮው ባለቤትነት ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦ የግንባታ ሥራው የተጀመረው የደረቅ ወደብ ሲጠናቀቅ የደብረ ብርሀን ከተማና የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያሳድጋል ብለዋል።


 

ደብረ ብርሃን ከተማ ከጅቡቲ ወደብ እና ከአዲስ አበባ ከተማ ባላት ቅርበት ምክንያት ምርትን በፍጥነት ከውጪ ወደሀገር ውስጥ ለማስገባትና ለማስወጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላት ገልጸዋል።

የወደቡ መገንባትም ተመራጭነቷን ይበልጥ ያሳድገዋል ብለዋል።


 

እንደ ሃላፊው ገለጻ የደረቅ ወደቡ ግንባታ ሥራ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅ በቀን ከ1ሺህ በላይ የጭነት ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው እንዳሉት፣ ከከተማው ፈጣን እድገት ጋር ተያይዞ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ ነው።


 

ለዚህም የደረቅ ወደብ ተርሚናሉ መገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ግንባታው በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊው እገዛና ትብብር ያደርጋል ብለዋል።

በተያያዘ ዜና የሰሜን ሸዋ ዞን መንገድ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መምሪያ ከ75 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጭ ያስገነባው የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።


 

በተርሚናል ግንባታ ሥራ ማስጀመሪያ ላይ ከክልሉ፣ ከዞንና ከደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የሥራ ሀላፊዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም