ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራና የተፈጥሮ ጥበቃ ስራዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ እያገዙ  ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18/2018  (ኢዜአ):- በኦሮሚያ ክልል የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራና የተፈጥሮ ጥበቃ ስራዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ እያገዙ እንደሚገኙ የክልሉ ደን እና ዱር እንስሳት ድርጅት አስታወቀ።

በክልሉ ደረጃ እየተካሄደ ያለው የካርበን ሽያጭ በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለሚደረገው ጥረት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል ደን እና ዱር እንስሳት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አራርሳ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ክልሉ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።

በተለይም የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን በመቀነስ የምድር ሙቀትን ለመግታትና የደን ሽፋን ለማሳደግ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመላክተዋል።


 

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉት ችግኞች መካከል አብዛኞቹ ጸድቀው ወደ ደንነት በመሸጋገራቸው የአካባቢውን አየር ንብረት በመጠበቅና የካርቦን ልቀትን በመቀነስ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ እያበሩከቱ ይገኛሉ ብለዋል።

ህብረተሰቡም ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ዘላቂ ተጠቃሚ የሚሆንበት አሰራር ተዘርግቶ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም አቅምን የማጠናከሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

አቶ አራርሳ ጨምረው እንደገለጹት፤ ክልሉ የደን ካርበን ንግድን በማስፋፋት በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ለሚደረገው ጥረት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በተደረገው ሳይንሳዊ ጥናት መሠረት አንድ ሄክታር የደን መሬት ከ10 እስከ 20 ቶን የሚደርስ ካርቦን ዳይኦክሳይድ በውስጡ የመያዝ እና የማመቅ ከፍተኛ አቅም እንዳለው አብራርተዋል።

ይህም ክልሉ የሚያካሂደው የደን ልማት ለአለም አቀፉ የካርቦን ልቀት ቅነሳ ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ማረጋገጫ እንደሆነ አብራርተዋል።

አቶ አራርሳ ኢትዮጵያ ከካርቦን ገበያ ገቢ ማግኘት የጀመረችበትን ታሪካዊ ሂደት ሲያብራሩ፤ የመጀመሪያው የደን ካርበን ሽያጭ እ.ኤ.አ በ2012 በባሌ ደን መጀመሩን አውስተዋል።

 እ.ኤ.አ ከ2012 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥም 9 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ካርቦን ለገበያ በማቅረብ ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተገኝቷል።


 

ከሽያጩ የተገኘው ገቢም ደኑን ለጠበቁ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ለቀጣይ የደን ልማት ስራዎች በመዋሉ የማህበረሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

ድርጅቱም ከአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ አጋሮች ጋር በመቀናጀት እ.ኤ.አ ከ2022 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት የተመዘገበውን 13 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርቦን መጠን ለገበያ ለማቅረብ ዝግጁ ሆኗል።

በቀጣይም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደኖችን በሳይንሳዊ መንገድ በመንከባከብና የካርቦን ንግድን በመተግበር የአካባቢ ጥበቃውን እንዲሁም ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን የማሳደግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም