በአማራ ክልል በመኸር ወቅቱ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በመኸር ወቅቱ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ በዘር ተሸፍኗል
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በመኸር እርሻ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም መልማቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንዬ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተያዘው የመኸር ወቅት የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ የተሻሻሉ አሰራርና ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርጓል።
ለዚህም ለአርሶ አደሩ በበቂ መጠን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ከማቅረብ ባለፈ በየደረጃው በሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ክትትልና ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት በኩታ ገጠም እርሻ ለማልማት ከ 3 ሚሊዮን 338 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማረስ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን እስካሁን በተደረገ ጥረት የእቅዱን 96 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።
የተሻሻሉ አሰራሮችን በመጠቀም በቆሎ፣ ስንዴ፣ ማሽላ ጤፍና በቆሎን ጨምሮ በ10 ዋና ዋና ሰብሎች በኩታ ገጠም የለሙ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 141 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
በኩታ ገጠም ለለማው ሰብል ከ3 ሚሊዮን 329 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና 212 ሺህ 381 ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ እንደዋለም ባለሙያዋ አስታውቀዋል።