ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ስራ አጥነትን ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዳማ ፤ነሐሴ 18/2018(ኢዜአ )፡-በኦሮሚያ ክልል ስራ አጥነትን ለመቀነስና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ በክህሎት ልማት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል ያለውን ከፍተኛ የወጣቶች ቁጥርና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የስራ ፈላጊዎች መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ዘላቂ የስራ ዕድል መፍጠር የክልሉ መንግስት ዋነኛ ትኩረት ሆኖ ቆይቷል።


 

ቀደም ሲል የሚደረጉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና የስራ ዕድል ፈጠራ ጥረቶች በቂ የቴክኒክና የክህሎት ክፍተት ባለባቸው ስራ ፈላጊዎች ምክንያት የተፈለገውን ያህል ውጤት ሲያመጡ አልታዩም።

በዚህም ምክንያት የክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ቢሮ ችግሩን ለመፍታት የሙያና ክህሎት ስልጠናዎችን እንደ ዋነኛ መሳሪያ በመጠቀም፣ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ አሰራር በመዘርጋት ላይ ይገኛል።

ዛሬ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የምክክር መድረክም፣ ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ዜጎችን በሙያና ክህሎት ለማብቃት የሚያደርገው የዚሁ ጥረት አካል ነው።


 

የቢሮው ሃላፊ ኢንጂነር ኤባ ገርባ በወቅቱ፤ ስራ አጥነትን ከመሰረቱ ለመቀነስ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ተኪ ምርት ለማምረት በሙያ የበቃ የሰው ሃይል በጥራትና በብዛት ማፍራት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የክልሉ ዜጎች በሙያ ራሳቸውን ችለው  ከመደበኛ ስራ በተጨማሪ በክህሎትና ኢንተርፕሩነርሽፕ ራሳቸውን ማጎልበት አለባቸው ብለዋል።

ገበያው የሚፈልገውን የሰው ሃይልና የሙያ ልማት ላይ መስራት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከግብርና፣ ትምህርት ፣ ማዕድን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ጨምሮ ከተለያዩ ሴክተሮች ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል።

የቢሮው የክህሎት ልማት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ነርሰዲን ቃድ በበኩላቸው የክህሎት ልማቱ መነሻ ገበያ ተኮር ሙያተኞችን ማፍራት ነው ብለዋል።


 

በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችንና አቅሞችን በመለየት የልማት ፕሮጄክቶች፣ ሆቴሎችና የቱሪዝም መስቦች እንዲሁም የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ ትኩረት አድርገን አጫጭር የሙያ ስልጠና እንሰጣለን ነው ያሉት።

በአዲሱ በጀት ዓመት ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ገበያ ተኮር አጫጭር የሙያና ክህሎት ልማት ስልጠናዎች 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች በመስጠት ወደ ስራ ለማስገባት መታቀዱን ለአብነት አንስተዋል።

ለዚህም በክልሉ 21 ዞኖችና 23 ከተሞች ያሉትን ፀጋዎችና የገበያ ፍላጎቶችን  በመለየት የክህሎት ልማት ስልጠና ይሰጣል ብለዋል።


 

በኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ የሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ፕሮግራሞች ዳይሬክተር እጩ ዶክተር መንግስቱ ለታ እንደገለፁት በሙያና ክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል ለማፍራት ከስራና ክህሎት ቢሮ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመን አብረን እየሰራን ነው ብለዋል።

"በአሁኑ ወቅት ለ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ተማሪዎች የክህሎት ትምህርት  እየተሰጠ ይገኛል" ያሉት ዳይሬክተሩ ለ11ኛ እና  12ኛ ክፍል ተማሪዎችም የሙያ ትምህርት ለመስጠት 23 የሙያ አይነቶች ተለይተው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም