በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በሳምንቱ መጨረሻ በተለያዩ ሀገራት በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸንፈዋል።
በሰሜን አየርላንድ ላርን ከተማ በተካሄደው የ“Antrim Coast Road Race” ውድድር፣ ዘንድሮ አዲስ በተካተተው የአምስት ኪሎ ሜትር ዘርፍ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይነቱን ይዘዋል።
በሴቶች 5 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት አይናዲስ መብራቱ ርቀቱን በ14 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ በመጨረስ አሸንፋለች።
የወንዶቹን 5 ኪሎ ሜትር ውድድር አትሌት ኤርሚያስ ግርማ በ13 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ በድል አጠናቋል።
በዚሁ ውድድር በሴቶች 21 ኪሎ ሜትር ግማሽ ማራቶን አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔር 1 ሰዓት ከ6 ደቂቃ ከ12 ሴኮንድ አንደኛ ወጥታለች።
አትሌት ውዴ ከፍያለው 1 ሰዓት ከ7 ደቂቃ ከ12 ሴከንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በወንዶች ግማሽ ማራቶን አትሌት ይስማው ድሉ 1 ሰዓት 1 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ አምስተኛ ወጥቷል።
በሌላ በኩል፣ በፓላንድ ሲሊሲያ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።
በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል አትሌት ገመቹ ጎዳና ርቀቱን በ8 ደቂቃ ከ2 ሴኮንድ አሸናፊ ሆኗል።
በሴቶች 1500 ሜትር አትሌት ፅጌ ዱጉማ 3 ደቂቃ ከ55 ሴከንድ በአስደናቂ አጨራረስ ድል ተቀዳጅታለች። በርቀቱም የዓመቱን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች።
በሴቶች 5000 ሜትር አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ርቀቱን በ14 ደቂቃ ከ54 ሴከንድ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።