ቼልሲ ከፉልሃም ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ቼልሲ ከፉልሃም ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 18 /2018 (ኢዜአ)፦ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጠናቀቃል።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ ፉልሃም ከቼልሲ በክራቨን ኮቴጅ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ፉልሃም ባለፈው የውድድር ዓመት በ52 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።
እ.አ.አ በ2025/26 የውድድር ዓመት ደካማ ብቃት ያሳየው ቼልሲ በ52 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ከአውሮፓ ውድድሮች ውጪ መሆኑም አይዘነጋም።
ቼልሲ የ44 ዓመቱ ዣቪ አሎንሶን፣ ፉልሃም በበኩሉ የ43 ዓመት አልቫሮ አርቤሎአን በአሰልጣኝነት መሾማቸው ይታወቃል።
ሁለቱ ስፔናዊ አሰልጣኞች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ያደርጋሉ።
በሊቨርፑል፣ ሪያል ማድሪድ እና ስፔን ብሔራዊ ቡድን አብረው የተጫወቱት አሎንሶ እና አርቤሎአ በአሰልጣኝነት ዳግም ተገናኝተዋል።
ሁለቱ የለንደን ክለቦች ከዚህ ቀደም በፕሪሚየር ሊጉ 38 ተገናኝተው ቼልሲ 23ቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል።
ፉልሃም አራት ጊዜ ድል ሲቀናው በቀሪ 11 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ቼልሲ በ38ቱ ጨዋታዎች ላይ 61 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ፉልሃም 28 ግቦችን አስቆጥሯል።
ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት እ.አ.አ ጃንዋሪ 2026 ላይ ሲሆን በክራቫን ኮቴጅ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ፉልሃም 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ፉልሃም በከተማ ተቃናቃኙ ላይ ተከታታይ የሊግ ድል ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።