በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ናቸው
ሚዛን አማን፣ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ):በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸውን የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እያካሔደ ነው።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ታሪኩ አካሉ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፣ የንግድ ሚዛን ሥርዓትን በማስጠበቅ ጤናማ ግብይት መፍጠር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
በዚህም በተጠናቀቀው የ2018 የበጀት ዓመት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚያስችሉ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን ይህም ውጤታማ እንደነበር ተናግረዋል።
ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል በተደረገው የክትትልና የቁጥጥር ሥራ 8 ሺህ በሚሆኑ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
ሕገ-ወጥ ንግድ የኑሮ ውድነትን የሚያባብስ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተግባሩ ላይ በተገኙ ነጋዴዎች ላይ በተወሰደው እርምጃ ከ52 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ መንግሥት ካዝና ገቢ ማድረግ እንደተቻለ አቶ ታሪኩ ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የቅዳሜና እሑድ ገበያ ማዕከላትን በማስፋፋት ኑሮን ለማረጋጋት ያለውን አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደ 36 ከፍ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።
የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው መለሰ፣ ከተማ አስተዳደሩ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የቅዳሜና እሑድ ገበያ ማዕከላትን ማደራጀት መቻሉን ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በመንግሥት የተነደፉ ኢንሼቲቮችን በአግባቡ መሬት ላይ በማውረድ ሸማቹን ከአላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ መታደግ ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል።
በምዕራብ ኦሞ ዞን የጀሙ ከተማ አስተዳደር ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ደምሴ በበኩላቸው፣ በከተማዋ ያሉ ሁለት የግብይት ማዕከላትን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በማዕከላቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ምርት የማቅረብ ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ የዋጋና ምርት መደበቅ ሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።