ቀጥታ፡

ለገበያው መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብና ገበያን በማረጋጋት ጉልህ ጠቀሜታ እያስገኙ መሆኑን ሸማቾችና ምርት አቅራቢዎች ገለጹ።

መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ማደራጀት አንዱ ሲሆን፣ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማኅበረሰብ እንዲደርሱ እያስቻለ ነው።

ገበያዎቹ አርሶ አደሮችና አነስተኛ አምራቾች ከደላላ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡ በማስቻል የገበያ ትስስርን አጠናክረዋል።

ይህም ለአምራቾች የተሻለ ገቢ እንዲፈጠር፣ ለተጠቃሚዎች ደግሞ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ በማድረግ የገበያ መረጋጋትን እያጎለበተ ይገኛል።

ኢዜአ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ሲሸምቱ ያነጋገራቸው ሸማቾች እንደገለጹት፣ ገበያዎቹ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በዓይነት፣ በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ በአቅራቢያቸው ማግኘት አስችለዋቸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ሶስና ገብረሚካኤል እንዳሉት፤ ገበያው በአቅራቢያቸው መከፈቱ ቀደም ሲል መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ለመሸመት ይባክን የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ ቀንሷል።

"አሁን የቅዳሜና እሁድ ገበያው በአቅራቢያችን በመኖሩ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ችያለሁ" ብለዋል።

መንግሥት በየአካባቢው ያስጀመራቸው የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እንግልትንና ወጪን በመቀነስ፣ የኑሮ ውድነትን ለማስታገስና ገበያን ለማረጋጋት የወሰደው ወሳኝ እርምጃ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በቀጣይም መንግሥት የሰብልና መሰል ምርቶችን በብዛትና በጥራት በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እንዲቀርቡ በማድረግ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ተጠቃሚ የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ዝናሽ ወጋየው፤ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የሚቀርቡ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ጥራት ያላቸውና ከመደበኛው ገበያ ከ20 በመቶ በላይ ቅናሽ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

መሰል ገበያዎች ለሸማቾች በቅርብ ከመገኘታቸው ባለፈ፣ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት የሚያስችሉ በመሆናቸው መጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የቅዳሜና እሁድ ገበያዎቹ የሸማቾችን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ በመቆጠብ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከታቸው ባለፈ ለዋጋ ንረት መረጋጋት ዓይነተኛ መፍትሔ መሆናቸውን አክለዋል።

በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የፍጆታ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው ለማኅበረሰቡ እፎይታ እየሰጠና የኑሮ ውድነትን እያረጋጋ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ቃልኪዳን ሰለሞን ናቸው።

ገበያዎቹ በየዕለቱ የምንጠቀምባቸውን መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች በአቅራቢያችን እንድናገኝ አስችለውናል ሲሉም ገልጸዋል።

በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ምርቶችን ለሽያጭ ይዘው ከቀረቡት መካከል ወጣት ሄኖክ ተሰማ፤ ምርቶችን በቀጥታ ከማሳ በማምጣት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቾች እያቀረቡ እንደሚገኝ ገልጿል።

አንዋር ሰዒድ በበኩላቸው፤ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የሚገበዩ ሸማቾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም