የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ የምድብ ሁለት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር ዛሬ ጨዋታውን ያከናውናል።
ጨዋታው ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከትናንት በስቲያ ባደረገው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ የጅቡቲውን ኡጄኮን 11 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።
ቡድኑ በጨዋታው ላይ ፍጹም የበላይነትን ወስዷል።
በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ለግማሽ ፍጻሜ ያልፋል።
በአንጻሩ የምድቡን የመጀመሪያ ጨዋታ የሚያደርገው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ሶስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።
ሁለቱ ክለቦች እ.አ.አ በ2024 በአዲስ አበባ በተካሄደው የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ማጣሪያ በግማሽ ፍጻሜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል።
ንግድ ባንክ በወቅቱ የማጣሪያ ውድድሩን በማሸነፍ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉ የሚታወስ ነው።
የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከነሐሴ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሩዋንዳ ኪጋሊ እየካሄደ ይገኛል።
በውድድሩ ላይ 10 ክለቦች በሶስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የማጣሪያ ውድድሩን ካሸነፈ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለሁለተኛ ጊዜ መሳተፉን ያረጋግጣል።
የሴካፋ ማጣሪያ እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
በ2026 የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ለመሳተፍ 36 ክለቦች በስድስት አህጉራዊ ዞኖች ተከፍለው የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።
በአህጉራዊ ቀጣናዎች በሚደረጉ ማጣሪያዎች አሸናፊ የሆኑ ክለቦች፣ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ የሞሮኮው ኤኤስ ፋር እና ውድድሩን የሚያዘጋጀው ሀገር ተወካይ ጨምሮ ስምንት ቡድኖች በዋናው ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።
የ2026 የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ዋና ውድድር አዘጋጅ ሀገር በቅርቡ በአወዳዳሪው አካል ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።