ሀገራዊ ምክክሩ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከር ሀገርን ለመገንባት አቅም የፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከር ሀገርን ለመገንባት አቅም የፈጠረ ነው
ጅግጅጋ፤ ነሀሴ 18/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከር ሀገርን ለመገንባት አቅም የፈጠረ መሆኑን የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
በሀገሪቱ የቆዩ ለአመግባባቶችን በምክክር ለመፍታት የተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በውጤት መጠናቀቁን የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከር ሀገርን ለመገንባት አቅም የፈጠረ ነው።
ምክክሩ በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ የመወያየትና የመነጋገር ባህልን በማጎልበት በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላምና እድገትን ለማምጣት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ከሀገር ሽማግሌዎቹ መካከል ሱልጣን አብዲ ኡስማን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመምከር መፍትሔን ማምጣት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በሀገሪቱ በጋራ ጉዳዮች ላይ በመምከር የተሻለች ሀገር ለመገንባት ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክሩ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች መሳተፋቸውና በሰከነ መንገድ መካሄዱ ለቀጣይም ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ሱልጣን አይደሩስ ጃማ በበኩላቸው ምክክሩ በሀገሪቱ ሠላምና ልማትን ለማስቀጠል የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ የተለያዩ ሀሳቦችን በማሰባሰብ በሠለጠነ መንገድ በውይይት የመፍታት ባህልን ያዳበረ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክክሩ በሀገሪቱ እድገትን ለማፋጠን መሰረት በመጣል የዜጎች ተጠቃሚነት እንዲጎለብትና ለትውልድ ምቹ ሀገርን ለማውረስ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ሰው ለሀገር ግንባታ አሻራውን የሚያሳርፍበትን መደላድል የፈጠረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሱልጣን አህመድ አቡበከር ናቸው።
ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራና የበለጸገች ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ሱልጣን ዩሱፍ ሂስ ኑር በበኩላቸው ሀገራዊ ምክክሩ በጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመወያየት መፍትሔን በማስቀመጥ በሀገሪቱ አዲስ የውይይት በር የከፈተ ነው ብለዋል።
ይህም ምክክር ጉዳዮችን በሀይል ከማስፈጸም በመውጣት በሠለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ባህልን ለማዳበር ልምድ የተወሰደበት ነው ብለዋል።