የመደመር መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠው የላቀ ትኩረት የቅርስ ከተማዋ ሀረር ልቃ እንድትታይ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠው የላቀ ትኩረት የቅርስ ከተማዋ ሀረር ልቃ እንድትታይ አስችሏል
ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ውብ እና አስደናቂ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል እና እሴቶች ባለቤት መሆኗ ይታወቃል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በቀረጽነው የለውጥ ፍኖተ ካርታ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል ድልብ የሆኑ የማህበራዊ እሴቶቻችንን በማጎልበት የማህበራዊ ልማታችንን ማጠናከር እና በአገሪቱ ያሉ የቱሪዝም ጸጋዎችን በማልማት የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ መገንባት ተጠቃሽ ናቸው።
በዚህ የለውጥ ዓመታት ጉዞ ውስጥ በበርካታ የአገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የህዝባችንን መልካም እሴቶች የሚያጠናክሩ፣ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚያስችሉ ባህሎቻችን እና እሴቶቻችንን ከማጎልበት ረገድ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ።
በተመሳሳይ ሁኔታ በሀገራችን ያለውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶችን በአግባቡ በመለየት፣ በማልማት እና በማስተዋወቅ ለሀገራችን መልካም ገጽታ ግንባታ እና ለማህበራዊ መስተጋብር መጎልበት ከአምስቱ የሀገራዊ ኢኮኖሚ ዋልታዎች አንዱ ሆኖ እየተሰራበት ይገኛል።
በዚህ ረገድ ከለውጡ ወዲህ በሀረሪ ክልል በማይዳሰስ ቅርስነት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ያስመዘገብነው የሹዋሊድ ባህላዊ ክብረ በዓል አንዱ ነው።
የአብሮነትና የአንድነት መገለጫ የሆነው እና የተዋበ ገጽታን የተላበሰው የሹዋሊድ አከባበር በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከህዳር 25 / 2016 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም አቀፍ የሰው ልጆች የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል።
ይህም ሐረርን በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ የሀገሪቱ ከተማ አድርጓታል።
ከዚህ በተጨማሪ ሀረር ከሰሃራ በታች ካሉ ከተሞች የመጀመሪያዋ የዓለም ቅርስ ከተሞች ድርጅት (Organization of World Heritage Cities) አባል ሆና መመዝገቧ የክልሉ መንግስት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱ የተግባር ማረጋገጫ ነው።
ሀረር ከተማ 115 ሀገራትን በአባልነት በያዘው የቅርስ ከተሞች ድርጅት እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ከሰኔ ወር 2023 ጀምሮ ነው የተመዘገበችው።
ሀረር የዓለም ቅርስ ከተሞች ድርጅት አባል ሆና መመዝገቧ በከተማዋ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብና ለማልማት እንዲሁም ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ የቅርስ ከተሞች በጋራ ጉዳዮቻቸውና ተሞክሮቻቸው እንዲለዋወጡ፣ በቅርስ ከተሞች የሚታየውን የመሰረተ ልማት ችግር እና የኢኮኖሚ ፈተናዎች ለመሻገር ብሎም ተያያዥ እድሎችን ለማስፋት የሚጠቅም ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ሐረር እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ከመጋቢት ወር 2025 ጀምሮ የዓለም ቱሪዝም ከተሞች ፌዴሬሽን አባል ሆናም ተመዝግባለች።
ሐረር የዓለም ቱሪዝም ከተሞች ፌዴሬሽን አባል ሆና መመረጧ ዘርፉ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ያግዛል።
የመደመር መንግሥት ቅርሶቻችን የዓለም እና የሀገር ኩራት እንዲሆኑ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል።