የሻደይ በዓል የህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነትንና ባህልን የማስተዋወቅ ከፍተኛ አቅም አለው - ኢዜአ አማርኛ
የሻደይ በዓል የህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነትንና ባህልን የማስተዋወቅ ከፍተኛ አቅም አለው
አዲስ አበባ፣ነሐሴ17/2018 (ኢዜአ):-የሻደይ በዓል የህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነትንና ባህልን የማስተዋወቅ ከፍተኛ አቅም እንዳለው የበዓሉ ታዳሚ ልጃገረዶች ገለፁ።
የ2018 ዓም የሻደይ በዓል በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ የአዲስ አበባ ነዋሪ የዋግህምራ አካባቢ ተወላጆች ተከብሮ ውሏል።
በዓሉን ሲያከብሩ ያገኘናቸው ልጃገረዶች ለኢዜአ እንዳሉት በዓሉ ሴቶች ልጆች ያለምንም ጫና፣ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆነው የሚደሰቱበት ልዩ የነፃነት መድረክ ነው።
የሻደይ በዓል በልጃገረዶች መካከል የጠበቀ ፍቅር፣ እህትማማችነት እና ማህበራዊ ትስስር እንዲጠናከር ያደርጋል ብለዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አስቴር ወልዴ ልጃገረዶቹ በቡድን በመሆን ከበሮ እየመቱና እጅግ የሚስቡ ባህላዊ የሻደይ ዜማዎችን እያዜሙ እንደሚያከብሩት ትናገራለች።
በዓሉ ሴቶች በነፃነት ወጥተው የሚጨፍሩበት የነፃነታቸው መገለጫ እንደሆነ በመግለጽ በዓሉን በአዲስ አበባ በጋራ ስናከብረው አንድነታችንን ያጠናክራል ነው ያለችው።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ቤተልሄም የኔው ሻደይ ሲከበር ሴቶች በተለያዩ ባህላዊ አልባሳት ደምቀው በነፃነት የሚያከብሩት በዓል መሆኑ ትናገራለች።
በዓሉ በአዲስ አበባ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ሲከበር በሕዝቦች መካከል ያለውን ግነኙነት የማጠናከር አቅም ስላለው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ትገልጻለች።
ሻደይ ተነፋፍቀው የነበሩ ሰዎችን በማገናኘት ናፍቆታቸውን የሚወጡበት አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን የገለጸችው ደግሞ እልፍ ወርቄ ናት።
በዓሉ የእርስበርስ ግንኙነት የማጠናከር አቅም ያለው በመሆኑ ይዘቱን ሳይለቅ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻዋን እንደምትወጣ ገልጻለች።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ እመቤት ተገኘ በበኩሏ በዓሉ ሴቶች ልጆች ያለምንም ጫና፣ ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆነው የሚደሰቱበት ልዩ የነፃነት መድረክ እንደሆነ ትገልፃለች።
የሻደይን በዓል በናፍቆት የምትጠብቀውና ለብዙ ጊዜ ሳታገኛቸው የቆዩ ጓደኞቿን የምትገናኝበት እንዲሁም ቱባ ባህሉን ያወቅኩበት ነው ያለችው ደግሞ ወይንሸት አበበ ናት።