ቀጥታ፡

የመሰረተ ልማት ግንባታና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች መዲናዋን ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ተመራጭ እንድትሆን አስችለዋል

አዲስ አበባ፣ነሐሴ17/2018 (ኢዜአ):-የአዲስ አበባ የመሰረተ ልማት ግንባታና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች መዲናዋን ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የጤና፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉባኤዎች ተመራጭ እያደረጓት መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት አበበ ገለጹ።

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያመጣቻቸው አበይት ለውጦች ለሌሎች ሀገራት በጥሩ ተሞክሮነት የሚጠቀሱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከናውነው የተጠናቀቁትና በመከናወን ላይ የሚገኙት የልማት ስራዎች የሀገሪቱንና የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ሁኔታ መቀየራቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መጋለቢያዎች፣ ሆቴሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾችና የመንገድ ማስፋፊያዎች በመገንባታቸው እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን አስችለዋል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ የመሰረተ ልማት ግንባታና የአካባቢ ጥበቃ ለውጥ መዲናዋን ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ የጤና፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉባኤዎች ተመራጭ አዘጋጅና አስተናጋጅ ማድረግ አስችለዋል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ አሁን ላይ የምስራቅ አፍሪካ የጤና ፌዴሬሽን ጉባኤን ጨምሮ የ76ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ኮሚቴ ስብሰባ በስኬት እያካሄደች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በጥቅምት ወር በርካታ ዓለም አቀፍ ተሳታፊዎች የሚገኙበትን ታላቅ የጤና መድረክ ጨምሮ፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪና በአረንጓዴ ዐሻራ ዘርፎች በርካታ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ አንስተዋል፡፡

ይህ ሊሆን የቻለው በኢትዮጵያ ምቹ የመሰረተ ልማት፣ ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ሆቴሎችና የላቀ የአገልግሎት አሰጣጥ እውን በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያመጣቻቸው አበይት ለውጦች ለሌሎች የአፍሪካና የዓለም ሀገራት በጥሩ ተሞክሮነት የሚጠቀሱ መሆናቸውንም አክለዋል።

ሁለንተናዊ ልማቱ አዲስ አበባ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችና ባለሙያዎች የሚገኙባት ብቻ ሳትሆን፣ ሕክምናው በምቹና ንጹሕ አካባቢ የሚሰጥበት የጤና ቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ማስቻሉንም እንዲሁ፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከበሽታ መከላከል ባሻገር የተሻለ የሕክምናና አክሞ የማዳን አቅምን በማሳደግ በኩል የጎላ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ 

በተደረጉ የቅርብ ጊዜ ጥናቶች መሰረት የሕክምና አገልግሎት መሻሻል የእናቶችና የሕፃናትን የሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የልማት ትሩፋቶችና የጤና ፖሊሲው ውጤታማነት የዜጎችን አማካይ በሕይወት የመኖር እድሜ እንዳሳደገውም አስታውቀዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም