የአረንጓዴ አሻራ ስኬት፦ኢትዮጵያን የአየር ንብረት ጥበቃ ሞዴል ያደረገ ኢኒሼቲቭ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ስኬት፦ኢትዮጵያን የአየር ንብረት ጥበቃ ሞዴል ያደረገ ኢኒሼቲቭ
የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በይፋ የተጀመረው በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ነው።
በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስከ አሁን ከ54 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ 32ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 32) እ.አ.አ በ2027 በኢትዮጵያ በሚካሄድበት ወቅት የተተከሉ ችግኞችን ብዛት 65 ቢሊዮን የማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ይገኛል።
አረንጓዴ አሻራ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ነው።ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የምግብ ምርታማነትን በማሳደግ፣ የደን ሽፋንን በመጨመር፣ የተራቆተ መሬትን ወደ ነባር ይዞታው እንዲመለስ በማድረግ እና አይበገሬ የአረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
በዚህም በ2011 ዓ.ም 17.2 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን፣ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በተከናወነው ሥራ ወደ 23.6 በመቶ ማደግ ችሏል።
ይህ ሀገራዊ እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እውቅና አግኝቷል።በሁለተኛው የዓለም የምግብ ሥርዓት ጉባኤ እንዲሁም በአዲስ አበባ በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ሥራዋን ያስተዋወቀች ሲሆን፣ የአፍሪካ ሀገራትም ለአህጉሪቱ ትልቅ ተምሳሌት የሚሆን ኢኒሼቲቭ ሲሉ አድንቀውታል።
ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን እንድታዘጋጅ መመረጧ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እያከናወነች ላለው ጥረት ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠበት እና የሀገሪቱን የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ውጤት የሚያሳይ ነው።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ችግኞችን በመለገስ የአካባቢ ጥበቃ የጋራ አጀንዳ መሆኑን በተግባር አሳይታለች።ይህም አረንጓዴ ዲፕሎማሲ በሀገራት መካከል በጎ ግንኙነትንና አዎንታዊ የቀጣናዊ ትስስር ድልድይን እየገነባ ይገኛል።
የድንበር ተሻጋሪ የወንዝ ተፋሰሶችን በመንከባከብ፣ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን ለጎረቤት ሀገራት በማዳረስ እና በጋራ ድንበሮች አካባቢ የደን ሽፋንን በማሳደግ ረገድ እያከናወነችው ያለው ሥራ አህጉራዊ ሰላምና ትብብርን የሚያጎለብት አዲስ የዲፕሎማሲ መንገድ ከፍቷል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች የአህጉሪቱን ፍላጎትና ጥቅም ለማስከበር ግንባር ቀደም ተሟጋች ሆናለች።
ለአየር ንብረት ለውጥ አነስተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ነገር ግን ለጉዳቱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጡ የአፍሪካ ሀገራት ፍትሃዊ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲያገኙ ድምፅ በመሆን አህጉራዊ መሪነቷን አስመስክራለች።
ይህም አፍሪካውያን በራሳቸው ሀገር በቀል መፍትሔዎች የአየር ንብረት ጥበቃን ማረጋገጥ እንደሚችሉ ማረጋገጫ ሆኗል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና አምባሳደሮች የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ ለአካባቢ ጥበቃ አርአያ የሚሆን ዓለም አቀፍ ሞዴል ሲሉ አድንቀውታል።
ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን ከመጠቀም፣የካርቦን ልቀትን ከመቀነስ እና ከኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መስፋፋት ጋር አጣጥማ የምታካሂደው እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤዎች ላይ እውቅና እንድታገኝ አስችሏታል።