የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን-ተመራቂ የጽናት ኮርስ ኮማንዶዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን-ተመራቂ የጽናት ኮርስ ኮማንዶዎች
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በአገኙት ስልጠና የሚሰጣቸውን ሀገራዊ ግዳጅ በውጤታማነት በመወጣት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን ከልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል የተመረቁ የጽናት ኮርስ መሰረታዊ ኮማንዶዎች ገለጹ።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ለ45ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን "የጽናት ኮርስ መሠረታዊ ኮማንዶዎች" በትናንትናው ዕለት አስመርቋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፉት መልእክት፤ የአየር ወለድና ኮማንዶ ኃይል በአካል ብቃቱ፣ በጽናቱና በከፍተኛ ወታደራዊ እውቀቱ የውጊያ አቅጣጫ ቀያሪ ኃይል መሆኑን ተናግረዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የጽናት ኮርስ መሠረታዊ ኮማንዶዎች ተመራቂ አባላት በበኩላቸው፤ በወሰዱት ስልጠና ከፍተኛ ወታደራዊ ልምድና ክህሎት መጨበጣቸውን ገልጸዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል መሠረታዊ ኮማንዶ አብዱልሰላም ስዩም ሀገር ያለ ሕዝብ፣ ሕዝብ ያለ ሀገር ተነጣጥለው ሊታዩ አይችሉም ብሏል።
የሀገርና የሕዝብ ሉዓላዊነት ተጠብቆ እንዲቆይ ደግሞ ከወታደሩ ብዙ እንደሚጠበቅ ገልጾ፤ሀገርን በመውደድ በወታደርነት ማገልገል ክብር በመሆኑ ባገኘው ወታደራዊ ስልጠና ሀገሩን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።
ኢትዮጵያን በውትድርና ሙያ ለማገልገል በጽናት የወሰደችውን ስልጠና በማጠናቀቋ መደሰቷን የተናገረችው መሠረታዊ ኮማንዶ ፋንታዬ ያደታ በበኩሏ፤ በወሰደችው ወታደራዊ ስልጠና ኢትዮጵያ በምትፈልጋት ሀገራዊ ግዳጅ ሁሉ ኃላፊነቷን በብቃት ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ሌላኛው ተመራቂ መሠረታዊ ኮማንዶ ዳግም ዳዊት፤ በስልጠና ቆይታው ብቃት ያለው ወታደር መሆን የሚያስችለውን ትምህርትና ልምድ ማግኘቱን ተናግሯል።
የስልጠና ሂደቱን በአግባቡ በማጠናቀቁ መደሰቱን ገልጾ፣በቀጣይም የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
መሠረታዊ ኮማንዶ ሙሉጌታ ግርማ ለውትድርና ያለው ልዩ ፍቅር ወደ ልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ገብቶ ስልጠናውን እንዲከታተል እንዳነሳሳው ገልጾ፤ በማዕከሉ ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን መውሰዱንና በቀጣይም ባካበተው ወታደራዊ አቅም የሀገሩን ዳር ድንበር ለመጠበቅ መዘጋጀቱን ተናግሯል።
መሠረታዊ ኮማንዶ ቃልኪዳን ጌታሁን በበኩሏ፤ በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል የወሰደችው ወታደራዊ ስልጠና ሀገሯን ለማገልገል ብቁ እና ዝግጁ እንዳደረጋት ገልጻ፣ ባካበተችው ወታደራዊ አቅም የሚሰጣትን ሀገራዊ ግዳጅ በውጤታማነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች።