የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ትብብራችንን ማጠናከር ይገባናል-ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ትብብራችንን ማጠናከር ይገባናል-ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ፣ነሐሴ17/2018 (ኢዜአ):-የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ ትብብራችንን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የ76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ የእግር ጉዞ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አካሂደዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መሐመድ ጃናቢ የአካል ብቃት እንቅስቃሴውን እና የእግር ጉዞውን አስጀምረዋል።
የእግር ጉዞው “ንግግርን ወደ ተግባር” (Walk the Talk) በሚል መሪ ሐሳብ ከአድዋ ድል መታሰቢያ ጀምሮ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ ተካሂዷል።
በወቅቱም ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ የአካል እንቅስቃሴ ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል አይነተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የአፍሪካ ሀገራት አክሞ ከማዳን ባሻገር ቅድመ መከላከል ስራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ አንድነታቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
በአፍሪካ ደረጃ ያለውን የጤና ዘርፍ አገልግሎት ለማጠናከር አባል ሀገራት አብሮ የመስራት ባህላችንን ማጎልበት ይገባናል ብለዋል።
የጤና ችግሮችን ለመፍታት ከመደበኛ የአዳራሽ ስብሰባ እና ከፅንሰ-ሃሳባዊ ውይይቶች ባሻገር በተግባር ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባም አክለዋል።
በጉባኤው ከሚነሱ ጉዳዮች በተጨማሪ፣ በተግባር የተደገፉና ሁሉንም ያቀፉ የጤና መፍትሔዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሀገራት በጋራ መስራት ለአህጉሪቱ የጤና ሉዓላዊነት መሰረት መሆኑን አብራርተው፤ እያንዳንዱ ሀገር ለሌላው አጋርነቱን በማረጋገጥ እና በመደጋገፍ መንፈስ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የጤና ሉዓላዊነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻለው የአህጉሪቱ ትብብር ተጠናክሮ ሲቀጥል መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ ሁሌም ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር መሐመድ ጃናቢ በበኩላቸው፤ የአህጉሪቱ ህዝቦች ተባብረው ከተነሱ ማሳካት የማይችሉት የጤና ግብ እንደሌለ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በአህጉሪቱ በየጊዜው የሚወሰዱ እርምጃዎችና የሚደረጉ የጋራ ጥረቶች በሙሉ ለወደፊቱ የአፍሪካ የጤና ዘርፍ የሚደረጉ ዘላቂ ኢንቨስትመንቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የአፍሪካ ብሩህ ነገ ዛሬ በሚወሰዱ ውሳኔዎች ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስገንዝበው፤ አህጉሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ዛሬ ላይ የተግባር ውሳኔዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡