ቀጥታ፡

በግሉ ዘርፍ ዘመናዊ ሆስፒታሎች መገንባታቸው ለከተማዋ የጤና ዕድገትና ለሜዲካል ቱሪዝም መስፋፋት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 17/ 2018(ኢዜአ)፦በግሉ ዘርፍ በርካታ ዘመናዊ ሆስፒታሎች መገንባታቸው ለከተማዋ የጤና ዕድገትና ለሜዲካል ቱሪዝም መስፋፋት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

‎ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተገነባውን ኒው ሊፍ ሜዲካል ኮምፕሌክስ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።





‎በምረቃ መርሃ ግብሩ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

‎ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በግሉ ዘርፍ በርካታ ዘመናዊ ሆስፒታሎች መገንባታቸው ለከተማዋ የጤና ዕድገትና ለሜዲካል ቱሪዝም መስፋፋት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።

በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ዘመናዊ ሆስፒታሎችን ሲመለከቱ ይቆጩ እንደነበር አስታውሰው፤ ባለፉት ዓመታት በግሉ ዘርፍ ይህን ቁጭት የሚቀይሩ ትላልቅ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

‎አዲስ አበባን የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ የሚያደርጉ ትላልቅ ዘመናዊ የጤና ተቋማት መገንባታቸውንም አስታውቀዋል።

‎አዲስ አበባን የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የኒው ሊፍ ሜዲካል ኮምፕሌክስ ተጨማሪ አቅም መሆኑን ገልጸዋል።



 

‎‎በአጠቃላይ በከተማዋ የተከናወኑት ተግባራት የከተማዋን ደረጃ የሚመጥኑና ሌሎች ሀገራትም የሚተማመኑበት የጤና ዘርፍ መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቁመው ይህ በጎ ጅምር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

‎በጤናው ዘርፍ የሚደረግ ኢንቨስትመንት መልሶ ሀገርንና ሕዝብን የሚጠቅም በመሆኑ በዘርፉ የሚደረግ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

‎የከተማ አስተዳደሩ በጤናው ዘርፍ ለተሰማሩ የግል ባለሀብቶች የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ በተከናወኑ ዘርፈ-ብዙ ተግባራት አበረታችና ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

‎ከጤና መሰረተ ልማት ግንባታ አንጻር በርካታ ስራዎች በመሰራታቸው የአገልግሎት ተዳራሽነትን ማሳደግ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።

‎በዘርፉ የሚታየውን እድገት የበለጠ ለማጠናከር የበርካታ አዳዲስ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት ግንባታ በስፋት እየተከናወነ ‎እንደሚገኝም ጨምረው አስታውቀዋል።


 

‎የኒው ሊፍ ሜዲካል ኮምፕሌክስ መስራችና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ኢማም አብዱራህማን በበኩላቸው፤ የህክምና ኮምፕሌክሱ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን አሟልቶ የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በቀጣይም ህብረተሰቡን ለማገልገል በጤናው ዘርፍ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም