ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ዘመናዊ ሽግግር፦ለአስተማማኝ የሕክምና አገልግሎት

ለዘመናት የሕዝብን ሕመም ተሸክመው፣ ሕይወትን በሕክምና ታድገው በርካታ ትውልዶችን ሲያገለግሉ የቆዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች ዛሬ ሁለንተናዊ መታደስና ዘመናዊነትን ተላብሰዋል።ከጊዜ ብዛት ያረጁ ሕንፃዎች፣ ጊዜ ያለፈባቸው የመሣሪያዎች እጥረትና መጨናነቅ የትናንት ገጽታቸው የነበረ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባካሄደው የጤና ዘርፍ ማሻሻያ አዳዲስ ሕንፃዎች፣ የላቁ የሕክምና ቴክኖሎጂዎችና የተቀላጠፈ የአገልግሎት ስሪት ተተክተዋል።

የዚህ ታሪካዊ ለውጥ ህያው ማሳያ የሆነው የራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል በግቢው ውስጥ በተገነባው ባለ ሰባት ወለል ዘመናዊ ማዕከል፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) የታገዙ ኤምአርአይ (MRI)፣ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድ፣ ተንቀሳቃሽ ኤክስሬይ እና በሰዓት 30 ሺህ ሊትር ኦክስጅን የሚያመርት ፕላንት ተገጥሞለታል።

በተጨማሪም ለሕክምና ባለሙያዎች የተዘጋጁ የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት፣ ዘመናዊ ቢሮዎች፣ የስብሰባ አዳራሾችና ካፌቴሪያዎች የሥራ አካባቢውን የላቀና ምቹ አድርገውታል።


 

ይህ የጤና ዘርፍ እድገት በአንድ ተቋም ብቻ ሳይወሰን፣ የሀገሪቱን የምርመራና የፍትሕ ሥርዓት አቅም ወደ አዲስ ደረጃ ያሸጋገረው የዘረመል (DNA)፣ የፎሬንሲክና የሥነ-ምርዛ ምርመራ የልህቀት ማዕከል እንዲሁም በቅርቡ ሥራ የጀመረው ላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የዚሁ ዘመናዊነት አካል ሆነዋል።

ላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተለይም የካንሰርና የልብ ሕክምናዎችን የሚያግዙ የላቁ ቴክኖሎጂዎች፣ በሰዓት 80 ሜትሪክ ኪዩብ ኦክስጅን የሚያመርት ፕላንት እና ባክቴሪያን የሚቋቋሙ (Anti-bacterial) የውስጥ ንጣፎች የተገጠሙለት ነው።

በተጨማሪም ዲጂታላይዝድ የተደረገው የታካሚዎች መረጃ አያያዝ ሥርዓት (EMR) አገልግሎቱን ፈጣንና ግልጽ ከማድረጉ ባሻገር፣ ከዚህ ቀደም ለከፍተኛ ወጪና እንግልት ይዳርጉ የነበሩ ውስብስብ ሕክምናዎችን በሀገር ውስጥ በመስጠት የሕክምና ቱሪዝምን ለመቀነስ ትልቅ መንገድ ከፍቷል።


 

ሆስፒታሎችን ማደስ ማለት አዲስ ሕንፃ መገንባት ብቻ ሳይሆን በታካሚዎች ላይ ተስፋን ማደስ፣ ለሐኪሞች የተሻለ የሥራ ከባቢ መፍጠርና ዜጎች ወደ ውጭ ሀገር ለሕክምና የሚሄዱበትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ በማስቀረት ሀገራዊ አቅምን ማሳደግ መሆኑን ኢቢሲ ዘግቧል።

በመሆኑም ቀደም ሲል በአሮጌ ሕንፃዎችና በነባር አቅም ይደረግ የነበረው ትልቅ አገልግሎት፣ ዛሬ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ምቹ መሠረተ ልማት ታግዞ የዜጎችን ሕይወት የመታደግ አዲስ የበጎ ምዕራፍ መክፈቻ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም