በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤታማ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤታማ ናቸው
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 17/2018 (ኢዜአ)፡- በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር በቅንጅት የተከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤት ማምጣታቸውን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክተል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ገለጹ።
የከተማ አስተዳደሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተከናወኑ የመንግስትና የፓርቲ ስራዎችን አፈጻጸም በመገምገም ላይ ይገኛል።
በመድረኩ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው እንደገለጹት፣ የከተማዋን ሰላምና ልማት ዘላቂ ለማድረግ በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አምጥተዋል።
በፖለቲካው ዘርፍም የመደመር መንግስት እሳቤዎችን መሰረት በማድረግ፣ አሰባሳቢ ትርክት የመገንባትና አሳታፊ የፖለቲካ መስመሮች መዘርጋታቸውን ጠቁመዋል።
ለአብነትም በ7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ህዝቡን በነቂስ ወጥቶ ይበጀኛል ያለውን መንግስት በመምረጥ ሀገርን ማስቀደሙን አሳይቷል ብለዋል።
ማህበራዊ ልማትን በማፋጠን ረገድም በትምህርት፣ በጤና እና የስራ አጥነት ችግርን በመፍታት ላይ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አቶ ጎሹ አመላክተዋል።
በከተማዋ ነዋሪዎች የቤት ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትም የቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን አንስተዋል።
የከተማዋን ገቢ ለማሳደግ የሚሰሩ የልማት ስራዎች፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲሁም የኮሪደር እና የጣና ዳር ልማት ፕሮጀክቶች በተሳካ ሁኔታ መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በከተማዋ የተመዘገቡትን ልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማስቀጠል ቅንጅታዊ ተግባራት በቀጣይም እንደሚጠናከር ገልጸዋል።
በመድረኩ በየደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።