ሕብረ ብሔራዊነት የተንጸባረቀበት የምክክር ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
ሕብረ ብሔራዊነት የተንጸባረቀበት የምክክር ጉባኤ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ሕብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት የተንጸባረቀበት እና ኢትዮጵያን ወደ የተሻለ ደረጃ የሚያራምድ መድረክ መሆኑን በጉባኤው የተሳተፉ ተመካካሪዎች ገለጹ።
በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች እንደተናገሩት፤ ሀገራዊ ምክክሩ አሳታፊና አካታች የሆነ እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት የተንጸባረቀበት መድረክ ነው።
በሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ተሳታፊ የነበሩት ተመካካሪ መሪማ ከማል እንደገለጹት፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው በስምንቱ አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ምክክር የተደረገበትና ሁላችንም ሀሳባችንን ያንጸባረቅንበት መድረክ ነበር።
ተመካካሪዎች ሀሳብና ጥያቄዎቻቸውን ያለተጽዕኖ በማቅረብ ምክክር የተደረገበትና ምክረ ሀሳቦች የቀረቡበት መድረክ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ ተክለሃይማኖት ገብረእግዚ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን ከአድዋ ድልና ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ ታሪክ የሰሩበት መድረክ ነበር ብለዋል።
በእስካሁኑ የኢትዮጵያ ታሪክ የተስተዋለው የጠመንጃ ጉዞ አውዳሚ መሆኑን በመገንዘብ የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር፣ ሌሎች ሀገራትም ችግራቸውን የፈቱበት መንገድ መሆኑን ተናግረዋል።
የምክክር ጉባኤው ሕብረ ብሔራዊነትና ኢትዮጵያዊነት የተንጸባረቀበት እና ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ የሚያራምድ መሆኑንም ገልጸዋል።ምክክሩ እኔነትን ትተን ሀገር ወዳድነትን ያስቀደምንበት፣ እንዲሁም አጀንዳንና ሀገርን ማዕከል ያደረገ ምክክር ነው ብለዋል።
ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ተቀራርበን በመመካከር ወደ መግባባት የመጣንበት ሂደት ነው" ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ ተመካካሪ ተስፋነሽ ኤርትሮ ናቸው።
የምክክር ጉባኤው ለትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን የምናስረክብበት ሂደት መሆኑንም አክለዋል።