ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ-የቀይ ባሕር ደህንነትና የቀጣናዊ መረጋጋት ዋስትና!

ኢትዮጵያ-የቀይ ባሕር ደህንነትና የቀጣናዊ መረጋጋት ዋስትና!

የቀይ ባሕር ቀጣና በዓለም አቀፍ የንግድ ዝውውር፣ በጂኦፖለቲካዊ ትስስር እና በባሕር ላይ ደህንነት ረገድ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ቦታ የሚይዝ ቀጣና ነው።ሆኖም በአሁኑ ወቅት አካባቢው የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች መራኮቻ፣የባሕር ላይ ወንበዴነት፣ የሕገ-ወጥ ንግድና የሽብር ስጋቶች የተጋረጡበት በመሆኑ፣ዘላቂ ሰላምና ደህንነቱን ለማረጋገጥ ጠንካራና አስተማማኝ አቅም ያለው ቀጣናዊ አጋር ያስፈልገዋል።ኢትዮጵያ በ130 ሚሊዮን ሕዝቧ፣ በገነባችው ግዙፍ ኢኮኖሚ፣በጠንካራ የመከላከያና የባሕር ኃይል አቅሟ እንዲሁም ቅድሚያ ለጎረቤት በሚለው የመደመር ዲፕሎማሲያዊ መርህዋ የቀይ ባሕርና የመላው ቀጣናው ደህንነት ዋስትና ሆና ወጥታለች።

ኢትዮጵያ ከራሷ ባለፈ ሀገራት ግጭት ሲያጋጥማቸው፣ለችግር ሲጋለጡ ቀድማ የምትደርስ፣ ሰላምን በማስከበርና መረጋጋትን በመፍጠር በጽኑ መሠረት እንዲቀጥሉ በማስቻል የምትታወቅ ሀገር ናት።በ1950ዎቹ የኮሪያ ጦርነት ወቅት የተባበሩት መንግሥታትን ጥሪ በመቀበል ከ3 ሺህ 500 በላይ ወታደሮቿን በመላክ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የፈጸመችው ገድል የቃኘው ሻለቃ በጦር ሜዳ ላይ ያሳየው ጀግንነትና የከፈለው መስዋዕትነት እስከ ዛሬ በዓለምና በደቡብ ኮሪያ ሕዝብ ዘንድ በከፍተኛ አክብሮት ይታወሳል። ይህ የሰላም ማስከበር ተሳትፎ ኢትዮጵያ አፍሪካን ጭምር ያኮራችበት ነበር።

ከዚያ በኋላም በኮንጎ፣በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በቡሩንዲ፣ በዳርፉር፣ በአብዬ እና በደቡብ ሱዳን ያበረከተችው አስተዋጽኦ በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደር የለሽ ሀገር ያደርጋታል።
በሶማሊያ ደግሞ ኢትዮጵያ የደም ዋጋ ከፍላ ሀገሪቱን በአሸባሪዎች ከመበታተንና ከመፍረስ ታድጋለች። የአልሸባብን ስጋት በመግታትና የሶማሊያን መንግሥት በመደገፍ ለቀጣናው ደህንነት የማይተካ ሚና ተጫውታለች። ዛሬም በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ዋነኛዋ ሀገር ሆና ቀጥላለች።ይህ የካበተ ልምድ ኢትዮጵያን የቀጣናው የደህንነት ዋስትና እንድትሆን አድርጓታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር እሳቤያቸው እንዳመላከቱት፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት ከሁሉም የውጭ ግንኙነቶች ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው። መደመር ከአጎራባች ሀገራት ጋር የምናደርገው ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅምን በአብዛኛው በጋራ ጥቅም ላይ ተመሥርቶ የሚመራ መሆን ይኖርበታል የሚል የጸና አቋም ያራምዳል። ዕጣ ፈንታችን የተሳሰረ ስለሆነ የጋራ ጥቅሞቻችንን መሠረት ያደረገ ትብብርና መተጋገዝ ያስፈልገናል የሚለው መርህም ኢትዮጵያ አሁን እየተራመደችበት ያለው የገቢር ነበብ ዲፕሎማሲ መገለጫ ነው።

ኢትዮጵያ በመደመር እያንዳንዱ የልማት እርምጃዋ፣ ቀጣናዊ መሻቷ ጎረቤቶቿን የሚያግዝና ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ጎረቤቶቿ ለችግር በተዳረጉ ጊዜም ቀድማ ደራሽ ናት። የሰላማቸው አምባ፣ የሀዘናቸው አጽናኝ ናት። ለአብነትም ሱዳን ከባድ ቀውስ ውስጥ በገባች ጊዜ 15 ሚሊዮን ዶላር በመደገፍ የችግር ጊዜ የአብሮነት መርሗን በተግባር አሳይታለች። በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ስደተኞችን በሯን ከፍታ ተቀብላ በማስጠለል ሰብዓዊ ኃላፊነቷን እየተወጣች ነው።ይህ ድርጊት ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿ ሕመም የሚያማት፣ እንደ ዋርካ ሆና የምታሳርፍ፣ ለጋራ ጥቅም ቀድማ የምትሰለፍ መሆኗን በግልጽ ያሳያል።

ኢትዮጵያ ወንዞቿና ጅረቶቿ የቀጣናውን ሀገራት የሚያለሙ፣ ለም አፈሯ ምግብ የሆናቸው ሀገር መሆኗም የማይታበል ሐቅ ነው። የመደመር መንግሥት ይህንን ተፈጥሯዊ ሚዛን በእሴት የጨመረ የትብብር ድልድይ አጽንቷል። በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመገንባት የቀጣናው የብርሃን ምንጭ እንዲሆን አድርጎታል። ግድቡ ለሱዳን፣ ለጅቡቲና ለኬንያ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ ትስስርን በማጠናከር የጋራ ልማትን እውን እያደረገ ነው። ኢትዮጵያ ሌሎች የኃይል ማመንጫዎችን በመገደብ የቀጣናውን የኃይል ዋስትና የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኝነቷን በተግባር እያሳየች ትገኛለች። ይህ በመደመር መንግሥት የሚተገበር ራዕይ ኢትዮጵያ የቀጣናው የጋራ የኢነርጂ ደህንነት ምሰሶ መሆኗን ያረጋግጣል።

የኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ የምግብ ሉዓላዊነትና የቀጣናው ተስፋ

የመደመር መንግሥት በተከተለው የጠራ እሳቤ ኢትዮጵያ ግዙፍ ኢኮኖሚ እየገነባች ነው። ይህም ትሩፋቱ ለቀጣናው ሀገራት ጭምር እየተትረፈረፈ ነው። በመሠረተ ልማት፣ በኢነርጂ፣ በኢንዱስትሪና በግብርና ዘርፍ የተከናወኑት ስኬቶች ሀገሪቱ የምግብ ዋስትናን በቀጣና ደረጃ ለማረጋገጥ ምሳሌ አድርጓታል።

የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በጀመረችው የስንዴ ልማት ኢኒሼቲቭ እመርታዊ ስኬት አስመዝግባለች። ለዓመታት በድርቅና በሌሎች ችግሮች የሚያጋጥማትን ሰብዓዊ ድጋፍ በእርዳታ ስትሸፍን የነበረችውና ለፍጆታ የሚሆን ስንዴንም ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት ስታስገባ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ ዛሬ ላይ በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር ስንዴን በበጋ መስኖና በክረምት በማልማት በዓመት 33 ሚሊዮን ቶን ስንዴ የምታመርት ሀገር ሆናለች። በአፍሪካ ቀዳሚዋ ስንዴ አምራች ሀገር፣ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በራሷ ምርት የተካች ሀገር፣ ለሌሎች ጎረቤት ሀገራት ስንዴ የምትልክ ሀገር በመሆንም እየተጠቀሰች ነው።
የምግብ ሉዓላዊነቷን በማረጋገጥ ጉዞዋ በመስኖ የሚለሙ መሬቶችን በከፍተኛ ሁኔታ በማስፋፋት፣ የክላስተር እርሻን በማጠናከር ኢትዮጵያ ከተረጂነት ራሷን ወደመቻል ተሸጋግራለች። ይህ የኢትዮጵያ ስኬት ለቀጣናው የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ተምሳሌት ሆኗል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት ድርቅን መቋቋም የሚችል የግብርና ሥርዓት በመገንባትና በረሃዎቿን በማልማት ምርትና ምርታማነትን አሳድጋለች። በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለተደጋጋሚ የድርቅ አደጋ ተጋላጭ ለሆነው ቀጣና ተግባራዊ ምሳሌን በአረንጓዴ አሻራ አሳይታለች። ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ሀገርን አረንጓዴ አልብሳለች። አረንጓዴ አሻራዋ ድንበር ተሻግሮ የቀጣናው የተስፋ ምንጭም ሆኗል።

የቀይ ባሕር ባለቤትነት ታሪካዊ መብትና የቀጣናው ደህንነት

ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት ቀይ ባሕርን ተፈጥሯዊ ወሰኗ በማድረግ የአዱሊስ፣ የምጽዋና የአሰብ ወደቦችን ስታስተዳድርና የንግድ ዝውውሩን ስታስጠብቅ የቆየች ሀገር ናት። በታሪካዊ አጋጣሚዎች ምክንያት ከባሕር ተገልላ የቆየች ቢሆንም፣ ለ130 ሚሊዮን ሕዝቧ፣ ለግዙፍ ኢኮኖሚዋ እና ለቀጣናው ደህንነት ሲባል የባሕር በር ማግኘት የህልውና ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን ዳግም በጥንካሬ በማደራጀት ስትራቴጂካዊ እርምጃ ወስዳለች። ይህ ዝግጁነት የቀይ ባሕርን የንግድ መስመር ከባሕር ወንበዴዎች ለመጠበቅ፣ የሕገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሣሪያ ዝውውርን እንዲሁም የሽብር እንቅስቃሴዎችን ከሥር ለማምከን የሚረዳ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነቷን በሰላማዊ መንገድ፣ በዲፕሎማሲና በጋራ ጥቅም መርህ ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት የመላው ቀጣናው አሸናፊነት ማረጋገጫ ይሆናል።

ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም፣ ልማትና መረጋጋት ቀዳሚ ሚናዋን ስታበረክት የቆየች የምስራቅ አፍሪካ ምሰሶ ናት።የኢትዮጵያ አቅምና ዝግጁነት ለቀይ ባሕር ቀጣና ደህንነት ዋስትና የሚሰጥ እንጂ ማንንም ሀገር የሚጎዳ አይደለም። በጋራ ጥቅም እና በቅድሚያ ለጎረቤት መርህ የሚሳካው የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መመለስ ለቀጣናው የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሎጂስቲክስ ቅልጥፍና እና ለጋራ ደህንነት መረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ ይጫወታል።

ዛሬም በመደመር እሳቤ፣ በጠንካራ ኢኮኖሚ፣ በጠንካራ የመከላከያ ኃይልና በቅድሚያ ለጎረቤት በሚሰጥ ጠንካራ ዲፕሎማሲ የቀጣናውን የተሻለ ነገ እየገነባች ነው። በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሳየችውን የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የቀይ ባህር ባለቤትነት መብቷን በማሳካትም ትደግመዋለች። የልማት ተስፋና የቀጣናው የደህንነት ዋስትናነቷን በገቢር ነበብነት ታረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም