ቀጥታ፡

ውበትን ከስልጣኔ ጋር ያቆራኙ የኮሪደርና የወንዝ ዳር ልማቶች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2018 (ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በኮሪደር እና በወንዝ ዳር ልማቶች የተገነቡት ቤተ መጽሐፍት እና የተለያዩ የመዝናኛ ስፈራዎች ለመጪው ትውልድ ብሩህ  ተስፋን የሰነቁ የስልጣኔ ማሳያዎች መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዲናዋን ዓለም አቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች፣ ለነዋሪዎቿ ምቹና ዘመናዊ ለማድረግ እያከናወነ የሚገኘው ግዙፍ የኮሪደር ልማት ስራ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ በማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት የኑሮ ዘይቤ ላይ አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።

ይህ በዋና ዋና አደባባዮች፣ መናፈሻዎች፣ መንገዶችና የወንዝ ዳርቻዎች ላይ ያተኮረው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፤ ውበትን ከጥቅም ጋር አዋህዶ የያዘ በመሆኑ  ከፍተኛ ለውጦችን እያመጣ ነው። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሉት፤ የተገነቡት የመጫወቻና የማንበቢያ ስፍራዎች የከተሜነት ምህዳሩን ከማሻሻላቸው ባሻገር ለወጣቶች የማሰላሰያና አዳዲስ ሐሳቦችን ማፍለቂያ ማዕከላት እየሆኑ ነው።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወይዘሮ ጺዮን ጌታቸው፤ በቅርብ ዓመታት የተከናወኑት የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች አዲስ አበባን ለኑሮ ተስማሚ ከማድረጋቸው ባሻገር፣ ነዋሪው አእምሮውን እያዝናና እውቀት እንዲገበይበት መንገድ መክፈታቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ግርማ አለሙ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቶቹ መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉና ለአዲሱ ትውልድ ጠንካራ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በተለይም የተዘጋጁት የንባብ ማዕከላት ለተለያዩ ጥናትና ምርምሮች ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።


 

የመዲናዋ ነዋሪ ወጣት ፍራኦል ናትናኤል በበኩሉ  የኮሪደር ልማቱ የሀገሪቱን መልካም ገጽታ በመገንባት በኩል የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ብሏል።


 

ይህም ለአገር ውስጥና ለውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጿል።


 

አቶ እንዲሪስ ተሾመ እና አቶ ግርማ ንጉሴ የተባሉ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ ደረጃቸውን የጠበቁ በርካታ  የመዝናኛ ስፍራዎች ተገንብተዋል ብለዋል። 

አሁን ላይ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የእረፍት ጊዜ ለማሳለፍ እነዚህን አካባቢዎች ምርጫቸው ማድረጋቸውን ተናግረዋል።


 

የወንዝ ዳርቻ ልማቶቹ፣ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍትና የመዝናኛ ስፍራዎቹ የከተማዋን ውበትና የህዝቡን የማህበራዊ ህይወት ደረጃ ያሳደጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም