የምክክር ጉባኤው በስኬት መጠናቀቅ በመደማመጥና መግባባት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ታሪካዊ መድረክ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው በስኬት መጠናቀቅ በመደማመጥና መግባባት ችግሮችን መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ታሪካዊ መድረክ ነው
መተማ፣ ነሐሴ17/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ በመደማመጥና መግባባት ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ታሪካዊ መድረክ መሆኑን የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ገለጹ።
በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምእራፍ የከፈተው የምክክር ሂደት አሳታፊ እና አካታች በሆነ መልኩ ለአመታት ተከናውኖ የምክክር ጉባኤ ተካሂዶ በትናንትናው እለት በስኬት ተጠናቋል።
የምክክር ሂደቱ በኢትዮጵያ የምክክርና የውይይት ባህል መሰረት ያኖረ ከመሆኑም በላይ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ዜጎች በአንድ መድረክ ተገናኝተውና ተቀራርበው መምከር የቻሉበት ነው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በምእራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የሚኖሩ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የምክክር ሂደቱ የትኛውንም ልዩነትና አለመግባባት በምክክር መፍታት እንደሚቻል አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ገልፀዋል።
በኮኪት ከተማ የሚኖሩት ሼህ ሱሌማን ምስጋና፤ ለአመታት የተመከረበት የምክክር ሂደት ስኬታማ በሆነ መልኩ መጠናቀቁ የግጭት ምእራፎችን በመዝጋት በምክክርና መግባባት ሀገር መገንባት የሚያስችለን ነው ብለዋል።
በሂደቱ የተመለከትነውም በጉዳዮች ላይ በመምከር ተደማምጦ በመግባባት ችግሮችን መፍታት የሚቻል መሆኑን ትምህርት የሰጠ ልምድ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የምክክር ውጤቶችን ተግባራዊ የማድረግ ሂደት የሁላችንም ትብብርና ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ያሉት ሼህ ሱሌይማን፤ ችግሮቻችንን በመፍታት ለቀጣዩ ትውልድ የምትመች ሀገር ለማስረከብ መትጋት አለብን ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ፍስሐ ምህረቱ፤ የምክከር ሂደቱ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን በራሳችን አቅምና በካበቱ እሴቶቻቸን መፍታት እንደምንችል በተግባር ያሳየንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ የፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጥልቀት በመምከር ስህተቶች ታርመውና መልካም ነገሮች ዳብረው እንዲዘልቁ የሚያስችል ስለመሆኑም አንስተዋል።
በመሆኑም ከዚህ በኋላ የግጭትና ጦርነት አዙሪት አብቅቶ በመግባባት ሀገር ለመገንባት ሁላችንም ልንዘጋጅ ይገባል ብለዋል።
ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪና የሀገር ሽማግሌ አቶ ይርጋ ተሰማ፤ እርስ በእርስ መደማመጥ ስንችል መፍትሔው እጃችን ላይ እንዳለ የምክክር ሂደቱ ጥሩ ግንዛቤ ሰጥቶናል ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይም የምክክር ባህልን ሰንቀንና የግጭት ልምምድን ቋጭተን ለሁላችንም የምትመች ሀገር መገንባት አለብን ብለዋል።
በምክክር ጉባኤው የተገኙ መልካም ልምዶችንና ስኬቶችን ወደ ተግባር በመቀየር የህዝቦችን ወንድማማችነትና የሀገርን ሰላም ለማፅናት ሁላችንም የጋራ ሃላፊነት አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ትናንት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን ለማጽናት የሚያስችል ታሪካዊ ሂደት መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል።