ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው የጸናች ሀገርን ለመገንባት መሰረት የጣለ ነው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 17/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የጸናች ሀገር እና በምክክር የሚያምን ትውልድ ለመገንባት መሰረት የጣለ መሆኑን የተለያዩ ተመካካሪዎች ገለጹ።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች እንደተናገሩት፤ ምክክሩ የተለያዩ ሐሳቦች በማሰባሰብ ለአዲስ ትውልድና ለሀገር ግንባታ መሰረት ለማስቀመጥ እድል የፈጠረ ነው።

ከተመካካሪዎቹ መካከል አይናለም ሙና እንደገለጹት፤ ጉባኤው የቆዩ ችግሮችን እና አለመግባባቶችን መፍታት የሚያስችሉ ሐሳቦችን ያቀበለ መድረክ ነው።

በጉባኤው በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸው፤ ምክክሩ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

ሀገራዊ ምክክሩ ለነገ ትውልድ መሰረት የሚሆኑ ሐሳቦች ላይ ጥልቅ ምክክሮችን በማድረግ ለችግሮች መፍቻ ቁልፍ መፍትሔ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ አቶ አዩ ከተማ ናቸው።


 

ሌላኛው ተመካካሪ አቶ ፈይሰል ጅብሪል ሀገራዊ ምክክሩ አካታች መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የጸናች ሀገርና በምክክር የሚያምን ትውልድ ለመገንባት መሰረት የጣለ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም