ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን መከሩ ኢትዮጵያም አሸነፈች-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የራሷን ዕድል በገዛ እጇ መወሰን እንደምትችል በተግባር አሳይታለች ሲል መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኢትዮጵያውያን መከሩ ኢትዮጵያም አሸነፈች ሲል ባስተላለፈው መልዕክት ፣ ኢትዮጵያ የኃይልና የግጭት ፖለቲካን በቃ በማለት ልዩነቶቿን በሰለጠነ የምክክር መድረክ ለመፍታት የወሰደችው እርምጃ፣ የሀገራችንን የፖለቲካ ምህዳር በአዲስ መሠረት ላይ የጣለ ታሪካዊ ድል ሆኗል ብሏል። 

በኢትዮጵያ የጥቂት ልሂቃን የጥቅም ድርድር የነበሩ የዝግ በር ልማዶችን የቀየረና፣ ሰፊውን ሕዝብ የውሳኔው ቀጥተኛ ባለቤት ያደረገ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል።

ዜጎች ለዘመናት ያጋጠሟቸውን ታሪካዊ ስብራቶች፣ ጥልቅ አለመግባባቶችና የሐሳብ ልዩነቶች በኃይል ሳይሆን በመደማመጥና በጋራ ጥበብ መፍታት እንደሚችሉ በተግባር አስመስክረዋል።

በሁሉም ክልልሎች ከቀበሌ እስከ ፌዴራል በተወከሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አርሶ/አርብቶ አደሮች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የብሔር-ብሔረሰቦች ተወካዮች እንዲሁም ምሁራንና ሊቃውንት በስምንት አጀንዳዎች ላይ ባደረጉት ሁሉን አቀፍ ውይይት የ130 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን ድምፅ አድምጠዋል። 

በዚህም ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በንግግር ብቻ መሆኑን ፍጹም አካታች በሆነ አርአያነት  አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከባንዳዎቸ ጋር ተጣምረው በዲጂታል ሚዲያ የሐሰት መረጃ ና ውዥንብር ለመፍጠር ቢሞክሩም፣ የምክክር ኮሚሽኑ ተቋማዊ ገለልተኝነቱን በጥብቅ ዲስፕሊን በመመራት በጽናት አስከብሯል። 

ከ54 በላይ የሚዲያ ተቋማትና 461 ጋዜጠኞች ሂደቱን በቀጥታ ሽፋን በመስጠት ትክክለኛ መረጃን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ችለዋል።

በልጆቿ ፍጹማዊ ጽናት በተከናወነው በዚህ ታሪካዊ ክንውን፣ኢትዮጵያ የራሷን ዕድል በገዛ እጇ መወሰን እንደምትችል በተግባር አሳይታለች!ኢትዮጵያውያን መከሩ ኢትዮጵያም አሸነፈች!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም