ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው በሰላም ፣በታላቅ የኃላፊነት ስሜት እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ተጠናቋል-የሠላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ

አዲስ አበባ ፣ነሐሴ 16/ 2018 (ኢዜአ)፦የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ታሪካዊ ሂደት በሰላም፣በታማኝነት፣በታላቅ የኃላፊነት ስሜት እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መጠናቀቁን የሠላም ሚኒስትር  አቶ መሐመድ እድሪስ  ገልፀዋል።

የሠላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ ለዘመናት የቆዩ መሠረታዊ ሀገራዊ ችግሮችን በሠለጠነ መንገድ በውይይት እና በምክክር ለመፍታት የተጀመረው ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን በማስመልከት ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ይህ ታሪካዊ ሂደት በሰላም፣ በታማኝነት፣ በታላቅ የኃላፊነት ስሜት እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መጠናቀቁን አድንቀዋል። 

ሀገርን ለማሻገር በብልሃት መክሮ፣ ትውልድን አስተሣሥሮ ሌላ ዓድዋ ሠርቶ ማለፍ መታደል ነው፤ ተከብሮ የመኖርን መሠረትም ያጸናል ሲሉ ጠቁመዋል።

ሀገራችን የመከረችበት ይህ ጉባኤ የሕዝብን አሸናፊነት፣ የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ የራስን ችግር በራስ የመፍታት ጥበብን እና የዓላማ አንድነትን በገሃድ ለዓለም ዳግም ያሳየ መሆኑንም አቶ መሐመድ እድሪስ አብራርተዋል። 

ይህም አዲስ የሽግግር ተስፋ ምዕራፍን የሚያመላክት ደማቅ ድል መሆኑን ነው የጠቆሙት።

በምክክሩ የተገኙ የጋራ መግባባቶችን እና የሰላም ፍሬዎችን መንከባከብ እና መጠበቅ የሁሉም ዜጋ የጋራ ኃላፊነት በመሆኑ፣ መላው ኢትዮጵያውያን ተባብረው የነገዋን ጠንካራ፣ የበለጸገች እና ሁለንተናዊ ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን መሠረት እንዲያጸኑ ሚኒስትሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም