ቀጥታ፡

የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልእክት

ኢትዮጵያ ስላሸነፈች እንኳን ደስ አለን!

ባለፉት 46 ቀናት ከሁሉም አካባቢና የህብረተሰብ ክፍል የተወከሉ አራት ሺህ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት ተጠናቅቋል፡፡ ስኬቱን የምንመዝነው በተሻገርናቸው ፈተናዎች፣ በተፈጠረው አዲስ ባህል እና በተግባባንባቸው ምክረ ሀሳቦች ነው፡፡

ምክክሩ ሁሉንም ጥያቄዎች በአንድ ጀንበር አይፈታም። ሁሉንም ቁስሎች አይፈውስም። ለሁሉም ቅሬታዎች ፍጹም መፍትሄ ሊያቀርብ አይችልም።

በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደታ የተፈጠሩ ችግሮችና ያልተመለሱ ጥያቄዎች ለዘመናት በየሥርዓቱ ሲዳፈኑ ኖረዋል፤ በኃይል ፍላጎትን ለማሳካትም ተሞክሯል። ይህ ደግሞ ቁስሎችን አባብሷል፤ ሀገራዊ ዕዳንም ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ አሸጋግሯል።

ሀገርን እግር ተወርች አስሮ የቀፈደዳትን ችግር በምክክር ለመፍታት ሲታሰብ ምክክሩ እንዳይጀመር፣ ሲጀመርም እንዳይቀጥል፣ ሲካሄድም እንዳይሳካ ብዙ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ሁሉንም ፈተና በጥበብና በትዕግሥት በማለፍ ኢትዮጵያ አሸንፋለች።

ኢትዮጵያውያን በልዩነታቸው ውስጥ መምከር፣ መደማመጥና መግባባት እንደምንችል ከእኛ ብዙ ለሚጠብቁ አፍሪካውያን በእርግጥም አስመስክረናል። በወሳኝ አጀንዳዎች ላይ መግባባት ተፈጥሯል፤ የቀሩ ሌሎች ጥያቄዎች ደግሞ ተጨማሪ ሥራ ይፈልጋሉ። ይህም የጉዞው አካል መሆኑን መረዳት ያሻል።

ለዘመናት ተከድነው የቆዩ፤ ታሽገው የቆሰሉ ብዙ ጉዳዮች ነበሩን፡፡ አየር ሲነካቸው የሚፈጠረው ችግር የሚጠበቅ ነው፡፡ የውይይት ባህል ከመዳከሙ ጋር ተደምሮ እንዲህና እንዲያ መባባሉ አያስገርምም፡፡ ዋናው ወደፊት መጓዛችን ነው፡፡ እየተግባባንና እየተሻገርን መቀጠላችን ነው፡፡ በመመካከራችን ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ዕንቅፋት በነበሩት ብዙ ጉዳዮች ላይ ተግባብተንባቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ከጫካ ወደ አዳራሽ፣ ከግርግር ወደ ምክክር የተዛወረ አዲስ ባህል ተፈጥሯል፡፡ ነገሮችን በሐሳብ እንጂ በጠመንጃ መፍታት እንደማይቻል፣ እንደማያዋጣም ታይቷል፡፡ ይህ አዲስ ባህል ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም፡፡ እያደገና እየተሻሻለ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልማድና መልክ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡

ይህ የምክክር ባህል አሁንም ገና ለጋ ነው። ጥበቃ፣ ልምምድ፣ ትዕግስት እና ድፍረት ይፈልጋል። እንቅፋቶች ይኖራሉ። ያከራከሩ ጉዳዮች ይኖራሉ። መልካም ጅምሮችን መውሰድ እና ይበልጥ ማሻሻል ይጠበቅብናል። ቅሬታዎቻችን ከጋራ ሀገራችን እንደማይበልጡ መተማመን ይኖርብናል።

ባለፉት 46 ቀናት ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን ከመጎሻሸም ይልቅ አብረን መምከር እንደምንችል አሳይተናል።

ይህ ምክክር እንዲሳካ ላደረጋችሁ ኮሚሽነሮች፣ ተመካካሪዎች፣ አመካካሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ ሚዲያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምስጋና ይገባችኋል፡፡ ታሪክ ምንጊዜም ሲያወሳችሁ ይኖራል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም