ቀጥታ፡

የሻደይ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል

ሰቆጣ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የሻደይ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሹመት ጥላሁን ገለጹ።

የሻደይ በዓልን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በአማራ ክልል የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሹመት ጥላሁን ገለፁ።

በሰቆጣ ከተማ "ሻደይ ባህላችንን እናከብራለን፤ እሴቶቻችንን እንጠብቃለን" በሚል መሪ ቃል የሻደይ በዓል በተለያዩ ኩነቶች በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
 
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሹመት ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ሻደይ ከቀደሙ አያቶች የተወረሰ የሰላም፣ የአንድነትና የሴቶች ነፃነት በይፋ መታወጁን የሚያበስር ታላቅ ባህላዊ እሴት ነው። 

በዓሉ የሴቶችን በራስ መተማመን ከማሳደግ ባለፈ በአካባቢው ፍቅርና አብሮነትን የሚያጠናክር በመሆኑ፣ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
 
የብሔረሰቡ የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ይርጋ ማርዬ በበኩላቸው፣ የአገው ሕዝብ ከኪነ-ሕንፃ አበርክቶው ጎን ለጎን የበርካታ የማይዳሰሱ ባህሎች ባለቤት መሆኑን ጠቅሰዋል።
 
ሻደይ የእኩልነትና የፍትህ ጥበብ ማሳያ በመሆኑ፣ ሳይበረዝና ሳይከለስ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በበዓሉ ላይ የተሳተፉት የፃግብጅ ወረዳ ተጫዋች ወጣት ዘውዲቱ ንጉሡ እና የሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ ተጫዋች ወጣት ብርቱካን አወጣ  በዓሉን በጉጉት የሚጠበቅና የአካባቢውን ባሕልና እሴተ ለማስተዋወቅ የጎላ ሚና አለው ብለዋል።
 
በዓሉን በፍቅርና በአንድነት እያከበሩት መሆኑን አመልክተው በዓሉን ለማክበር ያገኙትን ነፃነት፣ አብሮነትና ሰላም ለማስጠበቅ  እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
 
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ የሚከበረው የሻደይ በዓል፣ የታታሪነትና የለጋስነት እሴቶችን ባካተቱ የተለያዩ ባህላዊ ኩነቶች በደማቅ ሁኔታ መቀጠሉ ተመላክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም