ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጉዞ በድል ጀምሯል

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የምድብ ሁለት የማጣሪያ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጅቡቲው ኡጄኮን 11 ለ 0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።

በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ እሙሽ ዳንኤል አምስት ግቦችን አስቆጥራለች።

ረድኤት አስረሳኸኝ  እና ሊዲያ እያሱ  በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥሩ  እፀገነት ግርማ እና ታሪኳ ዴቢሶ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

በብርሃኑ ግዛው የሚመራው ንግድ ባንክ  በጨዋታው ፍጹም የጨዋታው የበላይነትን ወስዷል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ከዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር ያደርጋል።

ንግድ ባንክ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ለሁለተኛ ጊዜ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጉዞውን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውድድሩ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።

በሩዋንዳ ኪጋሊ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ትናንት መጀመሩ ይታወቃል።

የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም