ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው ጠንካራ ምክረ ሐሳቦች የተንሸራሸሩበትና የሕዝብን እውነተኛ ፍላጎት የሚያጸና ታሪካዊ መድረክ ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ጠንካራ ምክረ ሐሳቦች የተንሸራሸሩበትና የሕዝብን እውነተኛ ፍላጎት የሚያጸና ታሪካዊ መድረክ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የምክክር ጉባኤው ለአሁን ብቻ ሳይሆን የነገን ትውልድ የሚያሻግርና ሕብረ ብሔራዊነት የተንጸባረቀበት የዘመናዊ ሀገር ግንባታ ካስማ ታሪካዊ ስኬት መድረክ ነው።

ሀገራዊ ምክክሩ የጋራ ራዕይን ለማራመድ የሚያስችል የእውቀት መድረክ የፈጠረ፣ ውይይቱንም ወደ እርጋታና ስክነት ያሻገረ ነው ብለዋል።

የፖለቲካ ልምምድን ከቂምና ከበቀል ወደ ይቅርታና እርቅ ጎዳና፣ ከግጭትና ከነፍጥ አዙሪት በመላቀቅ ወደ ሰላማዊ ልምምድ ማሸጋገሩ እንዲሁም ማኅበራዊ መከባበርንና ሰከን ያለ ቋንቋን ማላመዱ ከምክክሩ ፋይዳዎች መካከል መሆኑን አንስተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሁላችንኢትዮጵያን የሚገልጹና የሚያጸኑ የጋራ መሻቶችን፣ እውቀትንና እጣ ፈንታን በአንድ ላይ ለማራመድ የሚያስችል ጠንካራ ሐሳብ የተንሸራሸረበት መድረክ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከጸብና ከደመኝነት ስሜት ወጥቶ በይቅርታ፣ በሰላምና በመደማመጥ ጎዳና እንዲራመድ መሠረት የተጣለበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

እያንዳንዱ ተዋናይ በወከለው ማኅበረሰብ ስም፣ በሀገር ጥላ ሥር በሕብረትና በመተሳሰብ የጋራ ጉዞን እንድንቀጥል የሚያስችል ሰፊ ዕድል የተመቻቸበትና የውይይት አቅም የታየበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጉዞ መስቀለኛ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው የድል፣ የዕድገትና የሕብረት መንገድ መሆን እንዳለበት እና የሚነሱ ሐሳቦች በሰላማዊ መንገድ መዳበር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

ሀገራዊ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ ብሎም ሰላምና ዕድገትን ለማረጋገጥ የሕብረተሰቡን ማኅበራዊ ትስስር፣ የጥንት ሥልጣኔ እውቀትና የጋራ እሴቶች ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ችግሮች የሚፈቱት በፖለቲካ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ግንኙነት፣ በመተሳሰብና በታሪካዊ የትዕግሥት እሴቶች ላይ ተመሥርቶ መሆን አለበት ብለዋል።

የምክክር ሂደት ጊዜያዊ የፖለቲካ መፍትሔዎችን ፍለጋ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ዕድገት የሚበጅ አዲስ የፖለቲካ ባህልን የሚያስተዋውቅና የሕዝብን እውነተኛ ፍላጎት የሚያጸና መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል።

የምክክሩ ሂደት በአንድ ጀምበር የተጠናቀቀ ሳይሆን እያደገና እየበለጸገ የሚሄድ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን እርምጃ ወደ ብልጽግና የሚያሻግር ሂደት ነውም ብለዋል።

የሂደት ዋነኛ ዳኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ሀገራዊ ፈተናዎችን በራሳችን ማኅበራዊ እሴትና ጥበብ በመፍታት የታሪክ ባለቤትነታችንን ማጽናት ለኢትዮጵያ ከፍታ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ጊዜያዊ የፖለቲካ መፍትሔ ፍለጋ ሳይሆን የኢትዮጵያን የፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዞ ወደ ብልጽግና የሚያሻግር ታላቅ ታሪካዊ ክንውን መሆኑ አብራርተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም