የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለአፍሪካ የሰላም ግንባታና የግጭት አፈታት ምሳሌ የሚሆን ነው - ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለአፍሪካ የሰላም ግንባታና የግጭት አፈታት ምሳሌ የሚሆን ነው - ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለአፍሪካ የሰላም ግንባታና የግጭት አፈታት ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሃ ግብር አካሂዷል
።
በዚሁ ወቅት የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የምክክር ጉባኤው አራት ሺህ የሕዝብ ወኪል ኢትዮጵያውያን ተመካካሪዎች የተሰባሰቡበት አሳታፊና ታሪካዊ ሂደት ነው ብለዋል።
የምክክር ጉባኤው ያለፈባቸው የዝግጅትና የትግበራ ምዕራፎችም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ልምድና ተሞክሮ የሚሆን የጋራ ሀገራዊ መግባባት መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት ከምክክር ውጭ የተሻለ አማራጭ የለም ያሉት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የኢትዮጵያውያን የምክክር ምክረ ሐሳቦችም ለዘላቂ ሀገር ግንባታ መሠረት ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያውያን ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በስኬት በመጠናቀቁ፣ አካታችና ሁሉን አሳታፊ ምክክር መካሄዱም ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን የጋራ መግባባት ተግባር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ሰላምን ለማምጣት መነጋገርና መመካከርን መምረጣቸው አስደናቂ ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።
ምክክር ጊዜ ቢወስድም ግጭትና ጦርነት ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር ጠቀሜታ አለው ያሉት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤም ሰላምን በማስፈን ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ መሠረት እንደሚሆን አስገንዝበዋል።