የኢትዮጵያ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት ባህል የምንጊዜም አፍሪካዊት ተምሳሌት ሀገር ያደርጋታል - የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት ባህል የምንጊዜም አፍሪካዊት ተምሳሌት ሀገር ያደርጋታል - የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት ባህል የምንጊዜም አፍሪካዊት ተምሳሌት ሀገር ያደርጋታል ሲሉ የኬኒያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የኬንያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ወቅት የማንነት ልዩነት ሳይገድባቸው ድል በማድረግ ለአፍሪካም ታሪክ ጽፋለች ብለዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ታሪክ የጽናትና የአይበገሬነት ምልክት ነው ያሉት ዑሁሩ ኬኒያታ፤ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ የነፃነት መንገድ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ማዕከል በመሆን አፍሪካን እያገለገለች እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም አዲስ አበባ አፍሪካውያን ለችግሮቻቸው የጋራ ምክክር የሚያደርጉበት ማዕከል ለመሆን መብቃቷን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለችግሮች ዘላቂ እልባት ለማበጀት ምክክር በማድረግ ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ታላቅ ገድል ፈጽማለች ብለዋል።
አፍሪካን ለሚገጥሟት ችግሮች የሰለጠነ አካሄድና ምክክር ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ አንድ እርምጃ በመራመድ አርአያነት ያለው ሥራ ማከናወን እንደቻለች ተናግረዋል።
ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ማበጀት አፍሪካ በሁሉም መስክ እንድትለወጥ መሠረት የሚጥል ነው ያሉት የኬኒያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዑሁሩ፤ የኢትዮጵያ የምክክር ጉባኤም የዚህ ምሳሌ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ምክክር በማድረግ ሰላምን መርጣለች፤ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤትና ለቀጣናውም ትልቅ ትሩፋት እንደሆነ አብራርተዋል።
በአፍሪካ የምንጠብቀውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በመፍጠር ብልጽግና እውን ለማድረግ የጥይት ድምጽ የማይሰማበት አህጉር መፍጠር ወሳኝ መሆኑንም አክለዋል።
ኢትዮጵያውያን፣ ዛሬ ያጠናቀቃችሁት የምክክር ጉባኤ ጅምር መሆኑን አምናለሁ ያሉት ዑሁሩ ኬኒያታ፤ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለማስረከብ በሚደረገው ጥረት ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።