የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን ለማጽናት የሚያስችል ታሪካዊ ሂደት ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን ለማጽናት የሚያስችል ታሪካዊ ሂደት ነው - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያን ለማጽናት የሚያስችል ታሪካዊ ሂደት መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመዝጊያ ስነ ስርዓት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ተመካካሪዎች የኢትዮጵያን ብዝሃነት በመወከል ላደረጉት ታሪካዊ ምክክር ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ብለዋል።
ሀገር ብርታት ጥበብና ብልሃቱ ምክክር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ምክክሩ ታሪካዊና ልዩ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ያከናወነውን ስራም አድንቀዋል።
ምክክሩ ምክንያታዊነትና ግልጽነት የተላበሰ እንዲሁም በመደማመጥና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መደረጉን አመልክተዋል።
ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያ ብዝሃነት ጎልቶ የታየበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ሀገራዊ ምክክር ነባር የኢትዮጵያ ባህል ቢሆንም መሬት ላይ ወርዶና የመዋቅር መልክ ይዞ እንዲካሄድ ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን ለማጽናት የሚያስችል ታሪካዊ ሂደት መሆኑንም ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።
ምክክሩ በሰከነ መንፈስ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል አዲስ ባህል የፈጠረ መሆኑንም አመልክተዋል።