የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን ከፈተና አውጥተው ወደ ተሻለና አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግሩ ጠቃሚ ምክር ሃሳቦች የፈለቁበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን ከፈተና አውጥተው ወደ ተሻለና አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግሩ ጠቃሚ ምክር ሃሳቦች የፈለቁበት ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያን ካለችበት ፈተና አውጥተው ወደ ተሻለና አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግሩ ጠቃሚ ምክር ሃሳቦች የፈለቁበት መሆኑን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ በማጠቃለያ ንግግራቸው፤ ይህ ታላቅ ጉባኤ በሀገራችን የፖለቲካና ማህበራዊ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያጋጠሟቸውን የአለመግባባት ስብራቶች በጋራ ጥበብ መፍታት እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጡበት አዲስ የፖለቲካ ባሕል መፈጠሩን ገልጸዋል።
በአሳታፊና አካታች የምክክር መድረኩ ላይ ከአራቱም የሀገር ማዕዘናት የተውጣጡ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በመሳተፍ ለኢትዮጵያ የሚበጁ ምክረ ሃሳቦችን ማዋጣት እንደቻሉ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የቀድሞ ታጣቂዎች፣ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የመንግሥት አካላትና ታዋቂ ሰዎች በአንድነት የተሰባሰቡበት ይህ መድረክ የመላው ኢትዮጵያውያን እውነተኛ የውይይት ማዕከል ነው ብለዋል።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገርና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት በሚያስችሉ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ምክክር መደረጉ አስረድተዋል።
ተመካካሪዎችም በሀገር ግንባታ፣ በመንግሥት አወቃቀርና ቅርጽ፣ በፌዴራል ከተሞች፣ በሃይማኖት፣ በተቋማት ግንባታ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች፣ በሰላም ግንባታ እንዲሁም በሙስና እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት መምከራቸውን አብራርተዋል።
በዐበይት አጀንዳዎች ላይ የተደረገው ምክክርም ቀላል እንዳልነበረና ጥልቅ የሐሳብ ልዩነቶች መስተዋላቸውን አንስተዋል።
የጉባኤው ትልቁ ስኬትም በልዩነቶች ውስጥም ቢሆን እርስ በርስ መደማመጥ፣ መከባበርና ለሀገር የተሻለ መፍትሔ በጋራ መፈለግ መቻሉ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተመካካሪዎቹ ሐሳብን በነጻነት በመግለጽ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ፈተና አውጥተው ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግሩ የላቁ ምክረ ሐሳቦችን በማመንጨት በቁርጠኛ ተሳትፎ ማድረጋቸውንም አድንቀዋል።
በዚህም የሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ተመካካሪዎች ኢትዮጵያን ካለችበት ፈተና አውጥተው ወደ ተሻለና አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግሩ ጠቃሚ ምክር ሃሳቦች ማፍለቅ የቻሉበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑን አንስተዋል።