ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ቡድን የካፍ የሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የማጣሪያ ጉዞ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ ስድስተኛው የካፍ የሻምፒዮንስ ሊግ በ2019 ዓ.ም ይካሄዳል።

በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ በስድስት ዞኖች 36 ክለቦች የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) ከዞኖቹ መካከል አንዱ ሲሆን በዚህ ዞን ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሴቶች ክለብ ጨምሮ 10 ክለቦች የሻምፒዮንስ ሊጉን ቦታ ለማግኘት ይፋለማሉ።

በሩዋንዳ ኪጋሊ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ውድድር ትናንት ጅማሮውን አግኝቷል።

በማጣሪያ ውድድሩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በምድብ ሁለት ከዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ እና ከጅቡቲው ኡጄኮ ክለብ ጋር ተደልድሏል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከጅቡቲው ኡጄኮ ክለብ ጋር ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ በኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈው የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።

በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ንግድ ባንክ የሴካፋ ዞን አህጉራዊ ማጣሪያ ከተጀመረበት ከእ.አ.አ 2021 አንስቶ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል።

እ.አ.አ 2021 እና በ2023 ውድድሮች እስከ ፍጻሜ ደርሶ በሁለተኝነት ያጠናቀቀው ንግድ ባንክ፣ እ.አ.አ በ2024 በአዲስ አበባ በተካሄደው የሴካፋ ማጣሪያ ግን ህልሙን እውን አድርጓል።

ቡድኑ በፍጻሜው የኬንያ ፖሊስ ቡሌትስን 1 ለ 0 በማሸነፍ የሴካፋ ዞን ቻምፒየን በመሆን፣ በታሪክ የመጀመሪያው በካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ዋናው የስምንት ቡድኖች ውድድር ላይ የተሳተፈ የኢትዮጵያ ክለብ መሆን ችሏል።

በሞሮኮ በተካሄደው ዋና ውድድር ከናይጄሪያው ኤዶ ኩዊንስ፣ ከደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሳንዳውንስ እና ከግብጹ ማሳር ጋር በምድብ ድልድል ተደልድሎ ተጫውቷል። ንግድ ባንክ በሶስቱም ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዶ ከምድቡ ማለፍ አልቻለም።

በሴናፍ ዋቁማ አማካኝነት ታሪካዊ የመጀመሪያ ግቡን የግብጹ ማሳር ላይ ያስቆጠረ ሲሆን ከካፍ የ150 ሺህ ዶላር የተሳትፎ ክፍያ ማግኘት ችሏል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታውን ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ከዩጋንዳው ካዌምፔ ሙስሊም ሌዲስ ጋር ያደርጋል።

ንግድ ባንክ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ ለሁለተኛ ጊዜ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጉዞውን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይኖርበታል።

የማጣሪያ ውድድሩ እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

በስድስት አህጉራዊ ቀጣናዎች በሚደረጉ ማጣሪያዎች አሸናፊ የሆኑ ክለቦች፣ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ የሞሮኮው ኤኤስ ፋር እና ውድድሩን የሚያዘጋጀው ሀገር ተወካይ ጨምሮ ስምንት ቡድኖች በዋናው ውድድር ላይ እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

የ2026 የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ ዋና ውድድር አዘጋጅ ሀገር በቅርቡ በአወዳዳሪው አካል ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም