ሀገራዊ ምክክሩ ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆን ነው -ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆን ነው -ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ለአፍሪካ ትልቅ ተምሳሌት መሆኑን የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመዝጊያ ስነ ስርዓት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።
የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉት አካላት በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው ሂደቱ ታሪካዊ መሆኑን አመልክተዋል።
አካታች እና ሁሉን አሳታፊ የሆነው ሀገራዊ ምክክር ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ሰላምን ለማምጣት መነጋገርና መመካከርን መምረጣቸው ሊያስመሰግናቸው ይገባል ብለዋል።
ለምክክር የሚወሰድ ጊዜ የትኛውንም ቢሆን ግጭትና ጦርነት ከሚያመጣው ጉዳት አንጻር አይተኬ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ምክክሩ በኢትዮጵያ ሰላም መስፈን ልማትና ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት የሚጥል ነው ብለዋል።