ቀጥታ፡

ማንችስተር ዩናይትድ ከአዲስ አዳጊው ሁል ሲቲ ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ አምስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 8 ሰዓት 30 ላይ ሁል ሲቲ ከማንችስተር ዩናይትድ በኤምኬኤም ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።

ሁል ሲቲ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ሊጉ መመለሱ ይታወቃል።

ክለቡ ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ ላይ የተወዳደረው .. 2016/17 ነበር።

በማይክል ካሪክ የሚመራው ማንችስተር ዩናይትድ ባለፈው የውድድር ዓመት 71 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በዘንድሮው የውድድር ዓመትም በጥሩ ግስጋሴው ለመቀጠል በመክፈቻ ጨዋታ አዲስ አዳጊውን ክለብ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በሊጉ 10 ጊዜ ተገናኝተዋል። ማንችስተር ዩናይትድ በስምንቱ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ማንችስተር ዩናይትድ 10 ጨዋታዎች ላይ 22 ግቦችን ሲያስቆጥር ሁል ሲቲ ሰባትጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ሁለቱ ክለቦች ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት .. 2017 ሲሆን በኦልትራፎርድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ያለ ግብ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

ሁል ሲቲ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ማንችስተር ዩናይትድን ለማሸነፍ ይፋለማል።

በሌሎች መርሐ ግብሮች ኢፕስዊች ታውን ከሰንደርላንድ፣ ኤቨርተን ከክሪስታል ፓላስ እና ኖቲንግሃም ፎረስት ከሊድስ ዩናይትድ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ብሬንትፎርድ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ ምሽት 1 ሰዓት 30 ላይ በጂቴክ ኮሚኒቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም