የኢትዮጵያ መከታ የሆነ አስተማማኝ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከታ የሆነ አስተማማኝ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል - ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በአስተማማኝነት የሚጠብቅ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል ሲሉ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል ለ45ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን "ፅናት ኮርስ መሠረታዊ ኮማንዶዎችን" በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአየር ወለድና ኮማንዶ ኃይል በአካል ብቃቱ፣ በፅናቱና በከፍተኛ ወታደራዊ እውቀቱ የውጊያ አቅጣጫ ቀያሪ ኃይል መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ኃይልና ኮማንዶ ኃይል አስቸጋሪ ፈተናዎችን ውስጥ አልፎ ሀገራዊ አደራውን በብቃት መወጣቱንም ገልፀዋል።
ተመራቂዎቹ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በታማኝነትና በቁርጠኝነት ማስከበር የሚችሉ ዝግጁ ኃይል በመሆን በተለመደው ጀግንነት ሀገራቸውን እንዲጠብቁም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ መከታ የሆነና በዘመናዊ ትጥቆች የተደራጀ አስተማማኝ የመከላከያ ሠራዊት መገንባቱንም ተናግረዋል።
የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ዛሬም በአስተማማኝ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን ሲሉም ነው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተናገሩት።